ኢትዮጵያ ከወጪ ንግድ ከ1 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ አገኘች 

በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሦስት ወራት ከወጪ ንግድ ከ1 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ ገልጸዋል።

ሚኒስትሩ የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የወጪ ንግድ (ኤክስፖርት) አፈጻጸምን ከላኪዎች ጋር መገምገማቸውን አስታውቀዋል።

አፈጻጸሙ በምርት ጭማሪም ሆነ በውጭ ምንዛሪ ዕድገት ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ለውጥ ማሳየቱን አመላክተዋል።

ይህም ከዕቅዱ 132 በመቶ መሳካቱንና ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አንጻር ከ700 ሚሊየን ዶላር በላይ ጭማሪ አለው ተብሏል።

በበጀት ዓመቱ ቀሪ ወራት የዕቅድ አፈጻጸሙን በማላቅ ኢኮኖሚው የሚፈልገውን የውጭ ምንዛሪ ግኝት ለማሳደግ ከዘርፉ ተዋናዮች እና ከላኪዎች ጋር የጋራ መግባባት ላይ መደረሱንም አመላክተዋል።

ይህ በዚህ እንዳለ ኢትዮጵያ ወደ ጎረቤት ሀገራት በላከችው የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ 31 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ገቢ ተገኝቷል ተብሏል።

ባለፉት ሦስት ወራት ለጎረቤት ሀገራት ከቀረበ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ 31 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታውቋል።

የኤሌክትሪክ ኃይል ለታንዛንያና ለደቡብ ሱዳን ለማቅረብ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን እንደገለጹት፥ በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሦስት ወራት 6 ሺህ 456 ጊጋ ዋት ሠአት የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት ለሀገር ውስጥ ፍጆታና ለጎረቤት ሀገራት ማቅረብ ተችሏል።

ይህም ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወራት ጋር ሲነጻጸር 36 በመቶ ብልጫ እንዳለው ገልፀዋል።

ገቢው ከዕቅዱ አንጻር የ91 ነጥብ 8 በመቶ አፈጻጸም እንዳለው አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ አሁን ላይ የኤሌክትሪክ ኃይል የማምረት አቅሟ ብሎም ከዘርፉ የምታገኘው ገቢ እድገት እያሳየ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

ኢትዮጵያ ለኬንያ፣ ጅቡቲ እና ሱዳን የኤሌክትሪክ ሀይል በመላክ ላይ የምትገኝ ሲሆን ለታንዛንያ 400 ሜጋዋት ሀይል ለመሸጥ ስምምነት ደርሰዋል።

እንዲሁም ለደቡብ ሱዳን የኤሌክትሪክ ሀይል ለመሸጥ የአዋጭነት ጥናት በመደረግ ላይ እንደሆነም ተገልጿል።

ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ከአፍሪካ በሀይል ማመንጨት አቅሙ ከፍተኛውን የሀይል ማመንጫ እየገነባች ሲሆን ከአንድ ዓመት በኋላ ይጠናቀቃል።

5ሺህ 200 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያለው ይህ የሀይል ማመንጫ አምስት ተርባይኖቹ ሀይል ማመንጨት ጀምረዋል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *