የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለአምስት ባንክ ላልሆኑ የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች የስራ ፈቃድ ሰጥቷል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሬ አገልግሎት እና ተደራሽነት ለማስፋት ከባንክ ጋር ከተያያዙ የውጭ ምንዛሬ ቢሮዎች በተጨማሪ ከባንክ ጋር ዝምድና የሌላቸው የግል የውጪ ምንዛሬ ቢሮዎችን ለመክፈት የሚያስችል የውጭ ምንዛሬ መመሪያ አውጥቷል፡፡
በዚህም መሰረት አምስት የግል የውጭ ምንዛሬ ቢሮዎች መስፈርት በማሟላታቸው የስራ ፍቃድ እንደተሰጣቸው ባንኩ ገልጿል፡፡
ፈቃድ ከተሰጣቸው ድርጅቶች መካከል ዱግዳ ፊደሊቲ ኢንቨስትመንት፣ ኢትዮ ኢንዲፔንደንት፣ ግሎባል፣ ሮቡስት እና ዮጋ ፎርኤክስ የተባሉ የግል የውጪ ምንዛሬ ቢሮዎች ናቸው፡፡
በመሆኑም ቢሮዎቹ ሙሉ ተቀባይነት ያላቸው እና የውጭ ሀገር ጥሬ ገንዘቦችን በመግዛት እና በመሸጥ እንዲሁም ከባንኮች ጋር በመቀናጀት ለወጪ እና ገቢ ንግድ የሚውል የውጭ ምንዛሬ በማመቻቸት ሚና እንደሚኖራቸው ተጠቁሟል፡፡
እንዲሁም በዋናነት የሚያካሂዱት የውጭ ምንዛሪ ሽያጭም ሆነ ግዢ ወዲያውኑ የሚፈጸም ብቻ ነው ተብሏል፡፡
በተጨማሪም ቢሮዎቹ ያለ ጉምሩክ ማረጋገጫ ከደንበኞች እስከ 10 ሺህ ዶላር፣ የጉምሩክ ፈቃድ ለሚያቀርቡ ደግሞ ከዚያ በላይ የውጭ ምንዛሬ በጥሬ ገንዘብ መግዛት እንደሚችሉ ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል፡፡
እንዲሁም የጉዞ መረጃ ላላቸው የግል ተጓዞች እስከ 5 ሺህ ዶላር እና ለንግድ ተጓዞች ደግሞ እስከ 10 ሺህ ዶላር በጥሬ ገንዘብ መሸጥ እንደሚችሉም ተገልጿል፡፡
ኢትዮጵያ ካሳለፍነው ሐምሌ ወር ጀምሮ የውጭ ምንዛሬ ተመን በገበያው እንዲመራ ማድረጓ ይታወሳል፡፡
በዚህ ውሳኔ ምክንያት የብር የመግዛት አቅም ከእጥፍ በላይ የቀነሰ ሲሆን አሁን ላይ አንድ የአሜሪካ ዶላር በ120 ብር እየተመነዘረ ይገኛል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) የሚመራው ብሔራዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ ዛሬ ባደረገው ስብሰባ የተደረገውን የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያዎች አፈፃፀም ገምግሟል።
ይህን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ፖሊሲው ተፈፃሚ በሆነባቸው ሁለት ወራት የተረጋጋ የውጭ ምንዛሪ ከባቢን መመልከት ችለናል” ሲሉ ገልጸዋል።
“በተመሳሳይ የገቢ ግባችን የተቀመጠለትን ግብ በመምታት በታለመለት መንገድ ላይ ይገኛል” ማለታቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።