ኢትዮጵያ ግዙፉን የሲሚንቶ ፋብሪካ አስመረቀች

አዲሱ የሲሚንቶ ፋብሪካ በቀን አንድ መቶ ሃማሳ ሺህ ኩንታል ሲሚንቶ የማምረት አቅም አለው ተብሏል፡፡

ፋብሪካው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት ተመርቋል፡፡

ፋብሪካው በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ልዩ ቦታው ለሚ ተብሎ በሚጠራው ቦታ የተገነባ ሲሆን ፋብሪካው ከአዲስ አበባ በ134 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ነው።

ተገንብቶ ለመጠናቀቅ ሁለት አመታትን ብቻ የወሰደው ፋብሪካ ዘመናዊ የሆነ ከሰው ንክኪ የራቀ ቴክኖሎጂ የሚጠቀም በመሆኑ የበለጠ ምርት ለማምረት የቀነሰ ኃይል የሚያስፈልገው ነው ተብሏል።

በተለይም 174 ሜትር ርዝመት ያለው በአለም ረዥሙ የሆነውን የቅድመ ማሞቂያ ማማ እንደያዘ በምረቃው ወቅት ተገልጿል።

የፋብሪካው የማምረት አቅም ከዚህ በፊት በማምረት ላይ ያሉ ተመሳሳይ ፋብሪካዎች ተደምረው የሚያመርቱትን ሃምሳ ከመቶ የሚያመርት ነውም ተብሏል።

ፋብሪካው በ2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር በጀት በኢትዮጵያው ኢስት አፍሪካ ሆልዲንግና በቻይናው ዌስት ኢንተርናሽናል ሆልዲንግ በሽርክና የተገነባ ነው፡፡

የኢስት አፍሪካን ሆልዲንግስ ሊቀ-መንበር ዶክተር ብዙአየሁ ታደለ ፋብሪካው ዘመኑ የደረሰበትን እጅግ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን የሚጠቀምና በግዝፈቱም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆኑን ገልጸዋል።

ፋብሪካው በኢትዮጵያ አሁን እየተመረተ ካለው የሲሚንቶ ምርት 50 በመቶ ያህሉን የመሸፈን አቅም እንዳለውም ሊቀመንበሩ ተናግረዋል።

ይህም የግንባታውን ዘርፍ በእጅጉ እንደሚያነቃቃ ጠቅሰው፤ በስራ ሂደትም በቀጥታና በተዘዋዋሪ ከ20 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የሰራ እድል እንደሚፈጥር አብራርተዋል።

ፋብሪካው በቀጣይ በአካባቢው ላይ የጂብሰም ቦርድና ተገጣጣሚ ቤቶች ማምረቻ ፋብሪካ ለመገንባት ዝግጅት ማጠናቀቁንም ሊቀመንበሩ ጠቅሰዋል።

በዘርፉ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎችን በማፍራት ረገድ ከተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ ባለሙያዎችን ቻይና በመላክ ማሰልጠኑን አውስተዋል።

በኢትዮጵያ 13 የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ያሉ ሲሆን አብዛኞቹ በአዲስ አበባ እና ኦሮሚያ ክልሎች የተገነቡ ናቸው፡፡

በአማራ ክልል የለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካን ጨምሮ ሁለት የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ሲኖሩ ድሬዳዋ ሶስት፣ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ትግራይ ክልሎች ደግሞ እያንዳንዳቸው አንድ ፋብሪካዎች አሏቸው፡፡

በአፍሪካ ግብጽ ፣አልጀሪያ፣ ናይጀሪያ እና ሞሮኮ ከአፍሪካ ቀዳሚ የሲሚንቶ አምራች ሀገራት ሲሆኑ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሰባተኛ ከምስራቅ አፍሪካ ደግሞ በአንደኛነት ተቀምጣለች፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *