አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እያንዳንዳቸው አምስት ሺህ ዶላር የሚያወጡ 30 ዘመናዊ ዲጂታል ብሬሎችን መረከቡን ገልጿል።
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከደቡብ ኮሪያው ሴሎም ኢንተርናሽናል ኮኦፕሬሽን ኤጀንሲ ጋር በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራርመው ነበር፡፡
በዚህ ስምምነት መሰረትም እያንዳንዳቸው አምስት ሺህ ዶላር የሚያወጡ 30 ዲጂታል ብሬሎችን እንደተረከበ አስታውቋል፡፡
ዩንቨርሲቲው እንዳስታወቀው በቀጣይ ደግሞ ተመሳሳይ ቀሪ 30 ብሬሎችን በድጋፍ እንደሚረከብ ገልጿል።
ይህ ዘመናዊ መሳሪያ ማየት የተሳናቸው የዩኒቨርሲቲያችን የቅድመ እና ድህረ-ምረቃ ተማሪዎች ከወረቀት ብሬል ተላቀው በቴክኖሎጂ በመታገዝ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ የሚረዳ ሲሆን፤ ከተለያዩ ዳታቤዞችም ጥናታዊ ጽሑፎችን ያለምንም ክፍያ አውረደው መጠቀም ያስችላቸዋል ተብሏል።
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአምስት አመት ስትራቴጂክ እቅዱ መሰረት ለዲጂታላይዜሽን ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቅድመ-ምረቃና በድህረ-ምረቃ ፕሮግራሞች ያስተማራቸውን ተማሪዎች ሰኔ 29 ቀን 2016 ዓ.ም ለ74ኛ ጊዜ በሚሊኒየም አዳራሽ እንደሚያስመርቅ አሳውቋል።
በኢትዮጵያ ካሉ ዩንቨርሲቲዎች አንጋፋው የሆነው አዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ በምርምር ስራዎች፣ ፋኩልቲ ብዛት እና ሌሎች የትምህርት መመዘኛ መሰረት አንደኛ ዩንቨርሲቲ ነው፡፡
ዓለም አቀፉ የዩንቨርሲቲዎች ደረጃ መዳቢ ማዕከል ከአንድ ወር በፊት ባወጣው ሪፖርት ምርጥ 2 ሺህ ዩንቨርሲቲዎችን ደረጃ ይፋ አድርጓል፡፡
በዚህም መሰረት ሀርቫርድ ዩንቨርሲቲ ምርጥ 1ኛ ዩንቨርሲቲ ሲባል ማሳቹሴትስ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት እና ስታንፎርድ ዩንቨርሲቲ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ዩንቨርሲቲዎች ተብለዋል፡፡
ከአፍሪካ ከአንድ እስከ 10ኛ ያለውን ደረጃ የደቡብ አፍሪካ ዩንቨርሲቲዎች ሲቆጣጠሩ ኬፕታወን ዩንቨርሲቲ፣ ዊትዋተርስራንድ ዩንቨርሲቲ እና ስቴለንስቦስች ዩንቨርሲቲ ከአንደኛ እስከ 3ኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡
ከኢትዮጵያ ስድስት ዩንቨርሲቲዎች ከዓለማችን ምርጥ 2 ሺህ ዩንቨርሲቲዎች ዝርዝር ውስጥ የተካተቱ ሲሆን አዲስ አበባ፣ ጎንደር፣ መቀሌ፣ ጅማ፣ ባህርዳር እና ሐሮማያ ዩንቨርሲቲዎች ተካተዋል፡፡
አዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ከአፍሪካ በ841ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ሲሆን ጎንደር ዩንቨርሲቲ በ1701ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ መቀሌ ዩንቨርሲቲ ደግሞ በ1748ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡