የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በ6ኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ ቀሪ ምርጫ በሚደረግባቸው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና አፋር ክልሎች እንዲሁም ድጋሚ ምርጫ በሚደረግባቸው በጅግጅጋ 2 እና መስቃንና ማረቆ ምርጫ ክልሎች በዛሬው ዕለት ምርጫ እየተካሄደ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ በ6ኛው ዙር ሀገራዊ ቀሪና ድጋሚ ምርጫ ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ ድምፅ መስጠት መጀመሩን አስታውቋል።
ዛሬ እየተካሄደ ባለው የድምጽ አሰጣጥ ሂደት ላይም 12 የፖለቲካ ፓርቲዎች እየተሳተፉ መሆኑን ከምርጫ ቦርድ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ቀሪና ድጋሚ ምርጫ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በአፋር፣ በሶማሌ እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች እየተካሄደ መሆኑንም ነው ቦርዱ ያስታወቀው።
ቀሪና ድጋሚ ምርጫ ከሚካሄድባቸው አካባቢዎች አንዱ በአፋር ክልል የሲሆን፤ በክልሉ 4 ዞኖች፣ በ9 የምርጫ ክልሎች እና በ388 የምርጫ ጣቢያዎች እየተካሄደ ነው።
ገዢው ፓርቲን ጨምሮ 4 የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚፎካከሩበት በዚህ ምርጫ ላይ ከ550 ሺህ በላይ ዜጎች እንደሚሳተፉ በምርጫ ቦርድ የክልሉ ምርጫ ማስተባበሪያ አስታውቋል፡፡
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልም ቀሪና ድጋሚ ምርጫው በ3 ዞኖች እየተካሄደ ሲሆን፤ በአሶሳ ዞን በአሶሳ ከተማ በሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች መራጮች ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በመገኘት እየመረጡ ነው።
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል 40 የምርጫ ጣቢያዎች የፀጥታ ችግር በመኖሩ በዛሬው ዕለት ድምፅ እንደማይሰጥም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ አስታውቋል
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመስቃን ወረዳ እና ማረቆ ልዩ ወረዳ ነዋሪዎችም ከማለዳው 12:00 ሰዓት ጀምሮ በድምጽ መስጫ የምርጫ ጣቢያዎች በመገኘት ድምፃቸውን በመስጠት ላይ እንደሚገኙ ኢዜአ ዘግቧል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ዋና ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ ትናንት በሰጡት መግለጫ ላይ፤ የፀጥታ ችግሮች ባለመስተካከላቸው አሁንም ምርጫ የማይደረግባቸው አካባቢዎች መኖራቸውም ተነስቷል።
የጸጥታው ሁኔታ ሲስተካከል የትግራይ እና አማራ ክልሎችን ጨምሮ በሌሎች ምርጫ ቦታዎች ምርጫ ለማካሔድ ቦርዱ ይሰራል ተብሏል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በ2013 እና በ2014 ዓ.ም በሁለት ዙሮች ሀገራዊ ምርጫ ያካሄደ ሲሆን በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ወቅት የጸጥታ እና የተዓማኒነት ችግር በነበረባቸው አካባቢዎች ድጋሚና ቀሪ ምርጫ ለማካሄድ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን ይታወሳል።
ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም በተካሄደው የኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ ምርጫ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫን ብልጽግና ፓርቲ 410 መቀመጫዎችን ያሸነፈ ሲሆን፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አምስት፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ አራት፣ በኦሮሚያ የተወዳደሩ ሦስት የግል ዕጩዎች፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አንድ ዕጩ፣ እንዲሁም በደቡብ ክልል የጌዴኦ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ሁለት መቀመጫዎችን አግኝተው ነበር፡፡
በአጠቃላይ በሁሉም የምርጫ ክልሎች 39 ሚሊዮን መራጮች ሲመዘገቡ 847 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደተደረገበት ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በወቅቱ አስታውቋል፡፡
በዚህ ምርጫ አሸንፈው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ከሆኑ መካከል አምስቱ በእስር ላይ ናቸው፡፡