በአማራ ክልል የተወሰኑ ወረዳዎች የባንክ አገልግሎት ተቋረጠ

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የፋኖ ሀይሎች በተቆጣጠሯቸውና ወጣ ገባ በሚሉባቸው ወረዳዎች የባንክ አገልግሎት ተቋርጧል፡፡

የፌደራል መንግስት የክልል ልዩ ሀይሎችን መልሼ አደራጃለሁ የሚል ውሳኔ ከወሰነበት ጀምሮ በአማራ ክልል በፋኖ ታጣቂዎች እና የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች መካከል ጦርነት ከተቀሰቀሰ አንድ ዓመት አልፎታል፡፡

በዚህ ጦርነት ምክንያት በክልሉ ለ10 ወራት የዘለቀ የአስቸኳይ አዋጅ የታወጀ ሲሆን ካሳለፍነው ሳምንት ግንቦት 28 ቀን 2016 ዓ.ም ጀመሮም የአዋጁ ጊዜ ቢያበቃም ክልሉ በኮማንድ ፖስት እየተዳደረ መሆኑን ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለም ካሳለፍነው ሳምንት ጀምሮ በሰሜን ሸዋ ዞን የተወሰኑ ወረዳዎች የባንክ አገልግሎት ተቋርጧል፡፡

የባንክ አገልግሎት ከተቋረጠባቸው ወረዳዎች መካከል መንዝ ላሎ፣ ግሼ ራቤል፣ አንፆኪያ ገምዛ እና ቀወት ወረዳዎች እንደሚገኙበት ዋዜማ ሬዲዮ ዘግቧል፡፡

ከወረዳዎቹ የባንክ ቅርንጫፎች የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው የባንክ አገልግሎቱን በተጠቀሱት ወረዳዎች እንዲያቋርጡ የተገደዱት የግል ባንኮች ጭምር ናቸው፡፡

በተጠቀሱት ወረዳዎች የባንክ አገልግሎት የተቋረጠው ካለፈው አርብ ሰኔ 7/2016 ዓ.ም ጀምሮ ነው ተብሏል፡፡ ከአርብ ጀምሮ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ስዓት ድረስ በመንዝ ላሎ ወረዳ ወገሬ ከተማ፣ በግሼ ራቤል ወረዳ ራቤል ከተማ፣ በአንፆኪያ ገምዛ ወረዳ መኮይ ከተማና ቀወት ወረዳ ራሳ ከተማ ባንኮች እንደተዘጉ ናቸው፡፡

አገልግሎቱ የተቋረጠው ባንኮቹ ድንገተኛ ትዕዛዝ ከመንግሥት አካል ከደረሳቸው በኋላ መሆኑን፣ የየወረዳዎቹ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የግል ባንኮች ሰራተኞች ተናግረዋል፡፡ ድንገተኛ የተባለው ትዕዛዝ ለባንኮቹ የተላለፈው የሸዋ ቀጠናን ከሚመራው ኮማንድ ፖስት እንደሆነም ተገልጿል፡፡

ባሳለፍነው ሳምንት በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሚዳወረሞ ወረዳ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሬማ ቅርንጫፍ  አካውንታችን ለምን ታገደ በሚል የተደራጁ ታጣቂዎች ወደ ባንኩ በመግባት 2,300,000 (ሁለት ሚሊዮን ሶስት መቶ ሺህ ብር) መውሰዳቸውን የወረዳው መንግስት ኮሙንኬሽን መግለጹ ይታወሳል።

ተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በኢትዮጵያ ስላለው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ዙሪያ ባወጣው ሪፖርቱ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ከተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ውስጥ 70 በመቶዎቹ በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች የተፈጸሙ ናቸው ማለቱ ይታወሳል፡፡

መንግስት ካሳለፍነው ነሀሴ እስከ ታህሳስ ባሉት አምስት ወራት ውስጥ በፈጸማቸው የድሮን ጥቃቶች ምክንያት 248 ንጹሃን ሰዎች ተገድለዋል ያለው የተመድ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሪፖርት እንደ ትምህርት ቤቶች እና ሆስፒታሎች አይነት የህዝብ መገልገያ ተቋማት ወድመዋልም ብሏል፡፡

በአጠቃላይ በኢትዮጵያ 594 የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደተፈጸሙ የተገለጸ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 70 በመቶ ያህሉ በመንግስት 22 ከመቶ አካባቢ ደግሞ በግጭቱ ተሳታፊዎች እንደተፈጸሙ ተገልጿል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *