በአማራ ክልል ጅጋ ከተማ 18 ሰዎች በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ተገደሉ

የጸጥታ ሀይሎቹ የአዕምሮ ህመምተኛን ጨምሮ በመዝናናት ላይ የነበሩ የባንክ ሰራተኞችን እና መምህራንን ገድለዋል

በአማራ ክልል፣ ምዕራብ ጎጃም ዞን፣ ጅጋ ከተማ፤ ቢያንስ 18 ሰዎች “በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች መገደላቸውን” ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡

ብሔራዊው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)፤ “በአካባቢው ጥቃት ተፈጽሟል” የሚል መረጃ እንደደረሰው ገልጾ ፤ ክስተቱን እያጣራ መሆኑን አስታውቋል።

የዓይን እማኞቹ፤ የጅጋ ከተማ ነዋሪዎች የተገደሉበት ክስተት የተፈጸመው ባሳለፍነው እሁድ ሰኔ 9፤ 2016 አመሻሽ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚሁ ዕለት ምሽት 11 ሰዓት ገደማ፤ የመከላከያ ሰራዊት አባላትን የጫኑ “ሶስት ፓትሮል” ተሽከርካሪዎች ከደንበጫ ወደ ጅጋ ከተማ እየገቡ በነበረበት ወቅት፤ “በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ የፋኖ አባላት” ከፊት በነበረው መኪና ላይ ጥቃት ካደረሱ በኋላ መሸሻቸውን የዓይን እማኞቹ አብራርተዋል።

ጥቃት ከደረሰበት መኪና ኋላ የነበሩ የመከላከያ ሰራዊት አባላት፤ በጥቃቱ “የወደቁትን አባሎቻቸውን” እነርሱ በነበሩባቸው ተሽከርካሪዎች ላይ ጭነው መሄዳቸውንም የከተማይቱ ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ከደቂቃዎች በኋላ “የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች” ወደ መሃል ከተማ በመምጣት፤ በዚያ የነበሩ ሰዎችን ጥይት በመተኮስ መግደላቸውን ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ነዋሪዎችን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል። 

ክስተቱን የተመለከቱ አንድ የዓይን እማኝ፤ “የመከላከያ ሰራዊት የደንብ ልብስ የለበሱ የጸጥታ ኃይሎች” በከተማው በሚገኘው ጎህ ሆቴል የነበሩ ሰዎችን “አስፓልት አስወጥተው ካሰለፏቸው በኋላ እንደገደሏቸው ተናግረዋል።

እኚሁ የዓይን እማኝ፤ በወቅቱ በሆቴሉ የነበሩ ፑል እና ከረንቡላ በሚጫወቱ እና በመዝናናት ላይ የነበሩ “የባንክ ቤት ሰራተኞች እና የባጃጅ አሽከርካሪዎች” እንደነበሩም ጠቁመዋል። በሆቴሉ የሚሰሩ ሴት አስተናጋጆችም፤ የሰዎቹን ማንነት “እየጮሁ ለማስረዳት” ሲሞክሩ እንደነበርም አክለዋል።

ግድያው የተፈጸመበት የጅጋ ምርጫ ክልል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ አበባው ደሳለው እንዳሉት በዕለቱ በጅጋ ከተማ  “በመከላከያ ሰራዊት አባላት እና በፋኖዎች መካከል” የተኩስ ልውውጥ መካሄዱን ተከትሎ 13 ሰዎች መገደላቸውን እና ሁለት ነዋሪዎች መቁሰላቸውን አስታውቀዋል።

የፓርላማ ተወካዩ እንዳሉት የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት በከተማዋ ሆቴል በመዝናናት ላይ የነበሩ የባንክ ሰራተኞች፣ አንድ የአዕምሮ ህመምተኛ ሴት እና አንድ መምህር ከሌሎች ሰዎች ጋር አብረው ከሚዝናኑበት ሆቴል ውስጥ አስወጥተው መንገድ ዳር በጥይት ተደብድበው ተገድለዋል ብለዋል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በኢትዮጵያ ስላለው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ዙሪያ ባወጣው ሪፖርቱ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ከተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ውስጥ 70 በመቶዎቹ በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች የተፈጸሙ ናቸው ማለቱ ይታወሳል፡፡

መንግስት ካሳለፍነው ነሀሴ እስከ ታህሳስ ባሉት አምስት ወራት ውስጥ በፈጸማቸው የድሮን ጥቃቶች ምክንያት 248 ንጹሃን ሰዎች ተገድለዋል ያለው የተመድ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሪፖርት እንደ ትምህርት ቤቶች እና ሆስፒታሎች አይነት የህዝብ መገልገያ ተቋማት ወድመዋልም ብሏል፡፡

በአጠቃላይ በኢትዮጵያ 594 የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደተፈጸሙ የተገለጸ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 70 በመቶ ያህሉ በመንግስት 22 ከመቶ አካባቢ ደግሞ በግጭቱ ተሳታፊዎች እንደተፈጸሙ ተገልጿል፡፡

የፌደራል መንግሥት ከአንድ ዓመት በፊት የክልል ልዩ ሀይሎችን “መልሼ አደራጃለሁ” የሚል ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ ነበር በአማራ ክልል ግጭት የተከሰተው።

ግጭቱ በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና የፋኖ ታጣቂዎች መካከል የተካሄደ ሲሆን ግጭቱ ተባብሶ መቀጠሉን ተከትሎ በአማራ ክልል ለስድስት ወራት የሚዘልቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ ይታወሳል።

ከሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ የታወጀው ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለተጨማሪ አራት ወራት ከተራዘመ በኋላ ከሁለት ሳምንት በፊት የተጠናቀቀ ቢሆንም ክልሉ አሁንም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመተዳደር ላይ ይገኛል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *