በየአራት ዓመቱ አንዴ የሚካሄደው የመላው ስፖርታዊ ውድድር ወይም ኦሊምፒክ የዘንድሮው ውድድር በፈረንሳይ ዋና ከተማ ፓሪስ ይካሄዳል።
ውድድሩ ከሐምሌ 19 ቀን 2016 ዓ/ም ጀምሮ የሚካሄድ ሲሆን ኢትዮጵያ በውድድሩ ከሚሳተፉ ሀገራት መካከል ናት።
በአትሌቲክስ ዘርፍ ኢትዮጵያን በውድድሩ ላይ የሚወክሉ አትሌቶች ምርጫ በስፔን ኔርሀ ትናንት ምሽት ተደርጓል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እንዳስታወቀው በ10 ሺህ ሜትር ሁለቱም ጾታ፣ በ1 ሺህ 500 ሜትር ወንዶች እንዲሁም በ800 ሜትር ወንዶች የማጣሪያ ውድድሮች ተካሂደዋል።
ኢትዮጵያ ለፓሪስ ኦሎምፒክ በ10 ሺህ ሜትር ወንዶች ውድድር ለመሳተፍ የማጣሪያውን ውድድርን በትንሹ በ27 ደቂቃ ማጠናቀቅን እንደ መስፈርት አስቀምጣለች።
በዚህም መሰረት በማጣሪያው ውድድር ከተሳተፉ 16 አትሌቶች ተሳትፈው ዮሚፍ ቀጄልቻ በ26፡31.01 1ኛ በሪሁ አረጋዊ 26፡31.13 2ኛ ፣ሰለሞን ባረጋ 26፡34.93 3ኛ እንዲሁም 4ኛ ቢንያም መሀሪ 26:37:93፣ 5ኛ ገመቹ ዲዳ 26:42:65 እና ታደሰ ወርቁ 26:46:80 6ኛ ሆነው አጠናቀዋል።
30:40 ዝቅተኛ መስፈርት በተቀመጠለት የሴቶች ተመሳሳይ ውድድር ከተሳተፉ 14 አትሌቶች ተሳትፈዋል።
በዚህም መሰረት የማጣሪያ ውድድሩን ፎትዬን ተስፋይ 29፡47.71 1ኛ ፣ፅጌ ገብረሰላማ 29፡49.33 2ኛ
እንዲሁም እጅጋየሁ ታዬ 29፡50.52 3ኛ እንዲሁም አይናዲስ መብራቱ በ30:09:05 4ኛ ሆና አጠናቃለች።
ሌላኛው የማጣሪያ ውድድር የተካሄደበት የ1500 ሜትር ወንዶች ውድድር ሲሆን ውድድሩ በተቀመጠለት የሚኒማ ሰዓት 3:33.50 መሰረት አብዲሳ ፈይሳ በ3:32.37 1ኛ እና ሳሙኤል ተፈራ በ3:32.81 2ኛ ሆነው ማጣሪያውን ያለፉ አትሌቶች ተብለዋል።
1:44:70 ሚኒማ በተቀመጠለት በ800 ሜትር ወንዶች ማጣሪያ ከተሳተፉ ሰባት አትሌቶች ውስጥ አንድም አትሌት መስፈርቱን ሳያሟላ ቀርቷል።
ኢትዮጵያ በኦሎምፒክ ታክ ስኬታማ ከሆኑ ሀገራት መካከል አንዷ ስትሆን ከ1948 ዓ.ም ጀምሮ በኦሎምፒክ ውድድሮች ላይ በመሳተፍ ላይ ናት፡፡
በአትሌቲክስ ዘርፎች ስኬታማ የሆነችው ኢትዮጵያ በአጠቃላይ 58 ሜዳሊያዎችን ስትወስድ ከዚህ ውስጥ 23ቱ ወርቅ 12 የብር እንዲሁም 23 የነሀስ ሜዳሊያዎች ናቸው፡፡
በ1952 ዓ.ም በጣልያን ሮም በተካሄደው የኦሎምፒክ ውድድር ላይ አበበ ቢቂላ በባዶ እግሩ ሮጦ የወርቅ ሜዳሊያ ያመጣ የመጀመሪያው አፍሪካዊ አትሌት ለመባል በቅቷል፡፡
እንዲሁም አትሌት ደራርቱ ቱሉ በስፔን ባርሴሎና በ1996 ዓ.ም በተካሄደው የኦሎምፒክ ውድድር ላይ በ10 ሺህ ሜትር ውድድር ወርቅ በማምጣት በኦሎምፒክ ውድድር ላይ ወርቅ ያመጣች የመጀመሪያዋ ጥቁር አትሌት ለመባል በቅታለች፡፡
አበበ ቢቂላ፣ ማሞ ወልዴ፣ ምሩጽ ይፍጠር፣ ሀይሌ ገብረስላሴ፣ ፋጡማ ሮባ፣ ገዛሀኝ አበራ፣ ሚሊዮን ወልዴ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ መሰረት ደፋር፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣ ቲኪ ገላና፣ አልማዝ አያና እና ሰለሞን ባረጋ በኦሎምፒክ ውድድሮች ላይ ለኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኙ አትሌቶች ናቸው፡፡