ኢትዮጵያ ለቀጣዩ ዓመት 1 ትሪሊየን ብር አመታዊ በጀት መደበች

የሚንስትሮች ምክር ቤት በ34ኛ መደበኛ ስብሰባው የ2017 በጀት አመት የፌዴራል መንግስት ረቂቅ በጀት አዘጋጅቷል።

የ2017 ዓ.ም የፌደራል መንግስት በጀት የአስር ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ አካል የሆነውን የ2016-2018 የልማትና ኢንቨስትመንት እቅድ ላይ የተቀመጡ ግቦችን እና የ2017-2021 የመካከለኛ ዘመን የማክሮ ኢኮኖሚና የፊስካል ማዕቀፍን ማስፈጸም እንዲቻል በሚያደርግ መልኩ መዘጋጀቱን አስታውቋል።

እንዲሁም የ2016 የፌደራል መንግስትን የፕሮግራም በጀት አፈጻጸም መነሻ በማድረግ፤ የመንግስት የፋይናንስ አቅም እና ተጠባቂ ገቢዎችን ታሳቢ በማድረግ እንዲሁም አስፈጻሚ መስሪያ ቤቶች የተሰጣቸውን ተልኮና ኃላፊነት ለመወጣት የሚያስፈልጋቸውን ወጪ በመገምገም እንዲዘጋጅ መደረጉንም የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

በዚሁ መሰረት ለፌዴራል መንግስት መደበኛ ወጪዎች ፣ ለካፒታል ወጪዎች ፣ ለክልሎች የሚሰጥ ድጋፍ፣ ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ድጋፍ እና ተጠባባቂ ወጪን ጨምሮ ወደ 1 ትሪሊየን የሚጠጋ በጀት ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ 

ምክር ቤቱ በቀረበው በጀት ላይ ተወያይቶ ‘ግብዓቶችን በማከል’ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል።

ኢትዮጵያ ከአንድ ወር በኋላ በሚጠናቀቀው የዘንድሮው 2016 ዓመት በጀት ዓመት 801.65 ቢሊዮን ብር መመደቧ ይታወሳል።

በሌላ ዜና ምክር የሚኒስትሮች ምር ቤት በዛሬው መደበኛ ስብሰባው የአረንጓዴ አሻራ እና የተጎሳቆለ መሬት ማገገሚያ ልዩ ፈንድን ማቋቋሚያ እና አስተዳደሩን ለመወሰን ረቂቅ አዋጅ ላይ ከተወያየ በኋላ ምክር ቤቱም ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ውሳኔ አሳልፏል።

የሚኒስትሮች ምር ቤት የነዳጅ እና ኢነርጂ ባለስልጣን እና የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ተቋማት ለሚሰጧቸው ልዩ ልዩ አገልግሎቶች የሚከፈሉ የአገልግሎት ክፍያዎችን ለመወሰን በቀረቡ ረቂቅ ደንቦች ተወያይቷል።

ምክር ቤቱም በረቂቅ ደንቦቹ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብአቶችን በማከል በነጋሪት ጋዜጣ ታትመው ከወጡበት ቀን ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውሉ ወስኗል።

ኢትዮጵያ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ከብድር እና እርዳታ 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ማግኘቷን የገንዘብ ሚኒስትር ከአንድ ወር በፊት መግለጹ ይታወሳል፡፡

ከተገኘው ገቢ ውስጥ 54 በመቶው ዕርዳታ ነው የተባለ ሲሆን 849 ሚሊዮን ዶላር በብድር የተገኘ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ከተገኘው ገቢ ውስጥም የዓለም ባንክ አንድ ቢሊዮን ዶላር ወደ ኢትዮጵያ ፈሰስ አድርጓል የተባለ ሲሆን ኢትዮጵያ ከዓለም ባንክ ጋር መልካም ግንኙነት እንዳላትም አስታውቃለች፡፡

ከሀገር ውስጥ ገቢ ለመሰብሰብ 356.5 ቢሊዮን ብር ለመሰብስብ ታቅዶ 338 ቢሊዮን ብር ገቢ እንደተሰበሰበም ተገልጿል፡፡

እንዲሁም ወደ ግል ይዞታ ከተዛወሩ የመንግስት ድርጅቶች በዘጠኝ ወር ውስጥ ከወቅታዊ እና ከውዝፍ ዕዳ ብር 760 ሚሊዮን ለመሰብሰብ ታቅዶ ብር 739 ሚሊዮን መሰብሰቡንም የገንዘብ ሚኒስቴር በሪፖርቱ ላይ ጠቅሷል፡፡

ከማዕከላዊ ግምጃ ቤት 470 ቢሊዮን ብር ክፍያ ተፈጽሟል ያለው የገንዘብ ሚኒስቴር  ለብሔራዊ ክልላዊ መንግስታት ለ2016 በጀት ዓመት ከተፈቀደዉ 153.5 ቢሊዮን ብር ተከፍሏልም ተብሏል፡፡

ኢትዮጵያ 29 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ብድር ያለባት ሲሆን ከዚህ ውስጥ ግማሹ ከቻይና የተገኘ ሲሆን የብድር መክፈያ ጊዜ እንዲራዘምላት በመጠየቅ ለይ ትገኛለች፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *