የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከአንድ ዓመት በኋላ ዳግም ተቀሰቀሰ

የትግራይ ታጣቂዎች ወደ አማራ ክልል ዘልቀው ወረዳዎን እና ቀበሌዎችን በሀይል እንደተቆጣጠሩ ተገልጿል፡፡

የአማራ ክልል መንግስት ባወጣው መግለጫ ህወሓት በፕሪቶሪያ የተፈረመውን የዘላቂ የሰላም ስምምነት በመጣስ ለአራተኛ ጊዜ ወረራ ፈጽሞብኛል ሲል ከሷል።

በፌደራል መንግስት በኩል ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር ውይይት ለማድረግ መጣሩን የገለጸው ክልሉ፣ ህወሓት የሰላም አማራጮችን ወደ ጎን በመተው በስምምነት አወዛጋቢ ተብለው የተለዩትን የራያ አላማጣ፣ የራያ ባላ፣ የኦፍላ፣ የኮረም እና ዛታ አካባቢዎችን ወርሯል ብሏል።

የክልሉ መንግስት እንዳለው ህወሓት ለአራተኛ ዙር ወረራ በመፈጸም በህወሓት እና በፌደራል መንግስት መካከል ከተካሄዱት “ከባለፉት ሶስት ዙር ደም አፋሳሽ ጦርነቶች” አለመማሩን የሚያሳይ ነው።

የአማራ ክልል ወረራ ተፈጽሞባቸዋል ያላቸው ቦታዎች እና የወልቃይት፣ ጠገዴ እና ጠለምት በ2013 ጦርነት ከመቀስቀሱ በፊት በትግራይ ክልል ስር የነበሩ እና የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደርም ጥያቄ ሲያነሳባቸው የነበሩ ናቸው።

ባለፈው መጋቢት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የአማራ ክልል መንግስት እነዚህን አወዛጋቢ ቦታዎች በመማሪያ መጽሀፍ ውስጥ ማካተቱን አውግዞ፣ የማያስተካከል ከሆነ ለሚፈጠረው ችግር ኃላፊት ይወስዳል ሲል አስጠንቅቆ ነበር

የአማራ ክልል መንግስት በጊዜያዊ አስተዳደሩ የወጣውን መግለጫ “ጸብ አጫሪ ነው” ሲል ነበር ምላሽ የሰጠው።

ክልሉ በዛሬ መግለጫው እነዚህ ቦታዎች ኢትዮጵያ በክልል አስተዳደር ከመዋቀሯ በፊት እና ከህገ መንግስቱ በፊት ህወሓት በኃይል የጠቀለላቸው ቦታዎች ናቸው በማለት በትግራይ በኩል የሚነሳውን ይገባኛል ጥያቄ አይቀበለውም።

ህወሓት “ስምምነቱን ሙሉ በሙሉ በመጣስ የተለያዩ ጥፋቶችን ሲፈጽም ቆይቷል፡፡አሁንም እየፈጸመ ይገኛል” ያለው የአማራ ክልል መንግስት በወረራ ይዟቸዋል ያላቸውን ቦታዎች ለቆ እንዲወጣ ጠይቋል።

ከሰሞኑ በራያ አካባቢዎች ተፈጥረዋል በተባሉ ግጭቶች በርካቶች መገደላቸው እና በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መፈናቀላቸው ተዘግቧል።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት በትናንትናው እለት ደቡብ ትግራይ በሚሉት አወዛጋቢ የራያ አካባቢዎች ያሉት ሁነቶች በስምምነት መሰረት እየተፈጸሙ ያሉ ናቸው ብለዋል።

አቶ ጌታቸው ከአማራ ክልል ወይም ከፌደራል መንግስት ወይም ከፌደራል መንግስት ጋር የተፈጠረ ግጭት ጋር የለም ሲሉ አስተባብዋል።

ግጭት እንዲፈጠር ያደረጉት በስም ያልጠቀሷቸው የፕሪቶሪያው ስምምነት ጠላቶች ናቸው ብለዋል አቶ ጌታቸው።

የፌደራል መንግስት ቀደም በእነዚህ አወዛጋቢ ቦታዎች ላይ ያሉ የአስተዳደር መዋቅሮችን እንደሚያፈርስ እና ቦታዎቹ በፌዴራል መንግስት ቁጥጥር ስር እንዲሆኑ እንደሚደረግ መግለጹ ይታወሳል።

የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸው አካባቢዎች በህዝበ ውሳኔ ወደፈለጉበት እንዲካለሉ የማድረግ እቅድ እንዳለውም የፌደራል መንግስት ገልጾ ነበር።

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የተጀመረው በ2013 ዓ.ም የትግራይ ታጣቂዎች በክልሉ በሚገኙ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን እዥ ላይ ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ ነበር፡፡

ለሁለት ዓመት በዘለቀው በዚህ ጦርነት ምክንያት ከአንድ ሚሊዮን በላይ ዜጎች ሲገደሉ 28 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ መሰረተ ልማቶች እንደወደመ የገንዘብ ሚኒስቴር ሪፖርት ያስረዳል፡፡

ጦርነቱ በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በተካሄደ ድርድር በፌደራል መንግስት እና በትግራይ ሀይሎች መካከል ተፈርሞ ቆሞ ነበር፡፡

በዚህ ስምምነት መሰረት የአማራ እና ትግራይ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸው አካባቢዎች በህገ መንግስቱ መሰረት በህዝበ ውሳኔ መፍትሄ ያገኛሉ የተባለ ቢሆንም የትግራይ ታጣቂዎች ቦታዎቹን በሀይል ለመንጠቅ ጦርነት ከፍተዋል ተብሏል፡፡

በጦርነቱ ሲሳተፉ የነበሩ ተዋጊዎችን ወደ ቀድሞ ህይወታቸው ለመመለስ ብሔራዊ የተሀድሶ ኮሚሽን የሚባል ተቋም የተቋቋመ ሲሆነ ገንዘብ በማሰባሰብ ላይ እንደሆነ ገልጾ ነበር፡፡

የአውሮፓ ህብረት የቀድሞ ተዋጊዎችን ወደ ቀድሞ ህይወታቸው ለመመለስ 16 ሚሊዮን ዩሮ እንደሚሰጥ የገለጸ ሲሆን የአፍሪካ ህብረት የሰላም ፈንድ ደግሞ አንድ ሚሊዮን ዩሮ እሰጣለሁ ብሎም ነበር፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *