ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የድምጻዊ አማኑኤል ሙሴ (ዝናር ዜማ) አልበምን ስፖንሰር አደረገ

ሰዋሰዉ መልቲሚዲያ እና ሳፋሪ ኮም ኢትዮጵያ በሙዚቃዉ ዘርፍ በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል።

ከ100 በላይ አንጋፋና ወጣት ድምፃዉያንን እና ሙዚቀኞችን ያስፈረመው ሰዋሰዉ መልቲሚዲያ እና ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በሙዚቃ አልበሞች እና በሁነቶች ዙሪያ በጋራ ለመስራት ተፈራርመዋል።

ከሰዋሰዉ ድምፃዉያን መካከል አንዱ የሆነዉ እና ከፋሲካ ፆም በኋላ የሚለቀቀዉን የአማኑኤል ሙሴ አልበም ሳፋሪ ኮም ኢትዮጵያ የስፖንሰርሺፕ ድርሻዉን ወስዷል።

በዝናር ዜማ የድምፃዉያን ስብስብ እራሱን ከህዝብ ጋር ያስተዋወቀዉ አማኑኤል ሙሴ  ‘’ጥቁር ዉሃ’’ የተሰኘዉ አልበሙም በሳፋሪኮም አጋርነት በሰዋሰዉ አፕ እንደሚለቀቅ ተገልጿል።

ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ከአማኑኤል ሙሴ በተጨማሪ ተስፋ የሚጣልባት ወጣት ሴት ድምፃዊ አልበምን ስፖንስር እንደሚያደርግ የተነገረ ሲሆን የድምፃዊቷን ማንነት ግን በቅርቡ ይፋ ይደረጋል ተብሏል።

ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የሙዚቃ አልበምን ስፖንሰር ሲያደርግ የአሁኑ የመጀመሪያው ሲሆን በቅርቡ ሁለተኛውን ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡

ድምፃዉያኑ በሰዋሰው መልቲሚዲያ በኩል ለአልበማቸዉ ከሚያገኙት ገንዘብ በተጨማሪ ከስፖንሰር አድራጊዉ ኩባንያም ክፍያ እና ልዩ የሆኑ ጥቅማ ጥቅሞችን ያገኛሉ ተብሏል፡፡

የሰዋሰዉ መልቲሚዲያ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሀብቱ ነጋሽ ድምፃዉያን የድካማቸዉን ዋጋ እንዲያገኙ ከዚህም በላይ መስራት ይጠበቅብናል ያሉ ሲሆን ፣ እንደ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ያሉ ግዙፍ ካምፓኒዎች ወደ ሀገራችን የሙዚቃ ኢንዱስትሪ መቀላቀላቸዉ ዘርፉን በሚገባ እንደሚደግፈዉም አንስተዋል።

ሰዋሰው መልቲሚዲያ አንድ ዓመት በሚጠጋ ጊዜ ውስጥ አንድ ሚልየን ተጠቃሚዎች ያፈራ ሲሆን ከዩኒቨርሳል ሙዚቃ ጋር አብሮ በመስራት ከ5 ሺህ የሚበልጡ አልበሞችን ወደ ሰዋሰው መተግበሪያ ለማስገባት እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

ሰዋሰው መልቲሚዲያ ከፋሲካ በዓል በኋላ የድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ጨምሮ ስድስት የሙዚቃ አልበሞችን ለአድማጮች እንደሚያደርስ ይጠበቃል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *