ኢትዮጵያን በአፍሪካ የአይሲቲ ውድድር የሚወክሉ ተወዳዳሪዎች ቱኒዝያ ገቡ

ዘጠኝ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በ8ኛው የሁዋዌ ክፍለ አህጉራዊ የአይሲቲ ውድድር ኢትዮጵያን ወክለው ለመወዳደር ቱኒዚያ ገብተዋል፡፡

በየዓመቱ የሚካሄደው የሁዋዌ አይሲቲ ውድድር በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ8ኛ ጊዜና በአገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ6ኛ ጊዜ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር እየተካሄ ይገኛል፡፡

የአገር አቀፍ ማጣሪያና ማጠቃለያ ውድድር ከተካሄደ በኋላ ዘጠኝ ኢትዮጵያውያን የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች አገራቸውን ወክለው በቱኒዚያ በሚካሄደው 8ኛው የሁዋዌ አይሲቲ ውድድር 2023-2024 ክፈለ አህጉራዊ የፍፃሜ ውድድር ላይ ለመሳተፍ ቱኒዚያ ይገኛሉ።

በውድድሩ ከዘጠኝ አገሮች ከተውጣጡ 90 ተማሪዎች ጋር የሚወዳደሩ ሲሆን እነዚህም አገራት ኢትዮጵያ፣ ማሊ፣ ካሜሩን፣  ሴኔጋል፣ አልጄሪያ፣ ቱኒዚያ፣ ሊቢያ፣ ግብፅ እና ሞሮኮ ናቸው።

ለዚህ አመት ውድድር ከ1,000 በላይ የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች የተመዘገቡ ሲሆን 280 ተማሪዎች ካሉበት ሆነው የአገር አቀፍ ውድድር ማጣሪያ ፈተና ላይ በኦንላይን ተሳትፈዋል።

ከእነሱም መካከል 80ዎቹ  በአገር አቀፍ የፍጻሜ ውድድሩ ተሳትፈው ዘጠኙ ለክፍለአሀጉሩ የሁዋዌ አይሲቲ የማጠናቀቂያ ውድድር ያለፉ ሲሆን ውድድሩም በቱኒዚያ ከየካቲት 28 እስከ መጋቢት 1 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ ይካሄዳል።

ሁዋዌ አይሲቲ ውድድር ለአለም አቀፍ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የተነደፈ የአይሲቲ ክህሎት ማሳደጊያና ማበልጸጊያ መድረክ ነው።

የሁዋዌ አይሲቲ ወድድር ጥራት ያለው የአይሲቲ ታለንት ዕድገትን ለማፋጠን፣ ለኢንዱስትሪው ብቁ ተሰጥኦዎችን ለማዘጋጅትና መምረጥ፣ የመስኩ ባለተሰጥኦዎችን ወደፊት ለማቅረብና ለዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ንቁ ተሳታፊዎችን ለማበርከት፣ የመስኩ ፍላጎትና አቅርቦት በቂ እንዲሆን ለማበረታታትና በዘላቂነት አስተዋፅኦ ለማድረግ የሚሰራ ነው።

በቱኒዝያ በውድድር የሚገኙት ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ ከጅማ፣ ከሐሮማያ እና አርባምንጭ ዩኒቨርስቲዎች የተገኙ ሲሆኑ ተማሪዎቹን ለማበረታታትም 3 መምህራን አብረው እንዲጓዙ ተደርጓል።

ከዚህ ቀድም በቻይና ሼንዘን ከተማ ከግንቦት 16 እስከ 20 ቀን 2015 ዓ.ም.  በተካሄደው 7ኛው የሁዋዌ ዓለምአቀፍ ውድድር ዘጠኝ ኢትዮጵያወያን ተማሪዎች ሦስተኛውን ሽልማት ማሸነፋቸው ይታወሳል። 

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *