አራት ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ባንኮች በኢትዮጵያ ለመሰማራት መፈለጋቸው ተገለጸ

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዳይሬክተር ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) በተቋሙ ስራ ዙሪያ በሰጡት መግለጫ ከየካቲት 4 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ዘርፍ መሰማራት ለሚፈልጉ የሀገር ውስጥ እና ውጭ ተቋማት ፈቃድ መስጠት ይጀመራል ብለዋል።

“እስካሁን ባለው ሂደት በርካታ ኢትዮጵያዊያን እና የውጭ ኩባንያዎች በኢንቨስትመንት ባንክ ለመሰማራት ፍላጎታቸውን አሳይተውናል” ያሉት ዳይሬክተሩ “ሶስት በዓለም አቀፍ ደረጃ ስም ያላቸው የውጭ ሀገር ኢንቨስትመንት ባንክ እና ሁለት የሀገር ውስጥ ተቋማት ፈቃዱን ለማግኘት እየጠየቁን ነው” ሲሉም ተናግረዋል።

ይሁንና ዋና ዳይሬክተሩ በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ባንክ ለማቋቋም ፍላጎታቸውን የገለጹት ዓለም አቀፍ ባንኮች ስም ዝርዝር ከመናገር ተቆጥበዋል፡፡

ዋና መቀመጫውን ደቡብ አፍሪካ ያደረገው እና በበርካታ የአፍሪካ ሀገራት ቅርንጫፍ ያለው ስታንደርድ ባንክ ባሳለፍነው ሳምንት በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ባንክ ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳለው ገልጾ ነበር፡፡

በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ባንክ ፍቃድ ለማግኘት ዝቅተኛው የተከፈለ ካፒታል ለዉጪ ባንኮች 100 ሚሊዮን ብር እና ከባንክ ላልሆኑ የፋይናንስ ተቋማት 25 ሚሊዮን ብር ሀብት ሊኖራቸው ይገባል።

ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በባንክ ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት ላላቸው የውጭ ባለሀብቶች አምስት የሚደርሱ የባንክ ፈቃድ ለመስጠት ማቀዷን ባሳለፍነው ግንቦት ወር ላይ ይፋ ማድረጓ ይታወሳል፡፡

ኢትዮጵያ በአጼ ሀይለስላሴ የአስተዳድር ዘመን በ1955 ዓ.ም የኢንቨስትመንት ባንክ ማቋቋም የሚያስችል ህግ ነበራት የተባለ ሲሆን እንደ ወንጂ ስኳር ፋብሪካ እና ሲሚንቶ ፋብሪካዎችን ጨምሮ ከ10 በላይ ተቋማት መመስረታቸው ተገልጿል።

ከ30 ዓመት በፊት ስልጣን ላይ የነበረው የደርግ ስርዓት በስራ ላይ የነበረውን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ህግ መሰረዙን ተከትሎ የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ሳይገቡ ተገድበው ቆይተዋል፡፡

ባለስልጠኑ አሁን ላይ የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪዎች ፈቃድ አሰጣጥ እና ቁጥጥር መመመሪያን አዘጋጅቶ ትግበራ መጀመሩንም ዳይሬክተሩ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) በመግለጫቸው ላይ ተናግረዋል።

በዚህ መመሪያ መሰረት አዋጭ የኢንቨስትመንት ሀሳብ አለን የሚሉ ነገር ግን የገንዘብ ችግር ያለባቸው ተቋማት በህግ እና ስርዓት ተወዳድረው ዓላማቸው እውን እንዲያዱርጉ የሚያግዝ ስርዓት መዘርጋታቸውንም ዳይሬክተሩ አክለዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም በቀጣዮቹ ስድስት ወራት ውስጥ አክስዮኖች ለህዝብ የሚሸጥበትን መመሪያ አዘጋጅተን ለህዝብ ይፋ እናደርጋለንም ብለዋል።

አስቀድመው ተቋቁመው አክስዮን በመሸጥ ላይ ያሉ ተቋማት ከኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን አሰራር እና ህግ ጋር እንዴት ይስተናገዳሉ? በሚል ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄም ” በገበያው ውስጥ አስቀድመው የገቡ እና አክስዮን በመሸጥ ላይ ያሉ ድርጅቶች ወደ አዲሱ የካፒታል ህግ እንዲካተቱ እና ድጋፍና ቁጥጥር እንዲያገኙ በቂ የሽግግር ጊዜ ይሰጣቸዋል” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

ይሁንና ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስቀድመው እውቅና ያገኙ የኢንቨስትመንት ባንኮች ከኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ሌላ የኢንቨስትመንት ባንክ ፈቃድ መውሰድ እንደማይችሉ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

“አክስዮን በመሸጥ ላይ ያሉ የተወሰኑ ድርጅቶች በሚዲያዎች ላይ የተጋነነ ትርፍ ማግኘት እንደሚችሉ የሚገልጹ አማላይ እና አሳሳች ማስታወቂያዎችን እያስተላለፉ መሆኑን ደርሰንበታል” ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ተጠያቂነትን ለማስፈን ከህግ እና ፍትህ ተቋማት ጋር እየመከሩ መሆኑንም ገልጸዋል።

የአክስዮን ሽያጭ እና ኢንቨስትመንት ባንክ ፈቃድን ለመስጠት ድርጅቶቹ የተቋቋሙበት መንገድ፣ የንግድ ፈቃድ፣ የደንበኞች ወይም ባለ አክስዮኖች ገንዘብ ዋስትና፣ የፋይናንስ እና ኦዲት ሪፖርትን ጨምሮ ሌሎችንም መስፈርቶችን በቅድመ ሁኔታነት እንደሚታዩም ተገልጿል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *