የኢትዮጵያ ኢሚግሬሽንና የዜግነት አገልግሎት እንዳስታወቀው የውጭ ሀገር ዜጎች ሀሰተኛ ሰነዶችን ተጠቅመው ወደ ሀገር ውስጥ መግባታቸውን ደርሼበታለሁ ብሏል፡፡
የኢሚግሬሽንና የዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት በሰጡት መግለጫ በርካታ የውጭ ሀገር ዜጎች ሀሰተኛ ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ፣ ሀሰተኛ ጊዚያዊ የመኖሪያ ፈቃድ፣ ሀሰተኛ ፓስፖርት፣ ሀሰተኛ ቪዛ እና ሀሰተኛ ሰነድ አዘጋጅተው በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች እየኖሩ ይገኛል ብለዋል።
በተደረገው የማጣራት ስራ ከ18 ሺህ በላይ ሀሰተኛ ጊዚያዊ የመኖሪያ ፈቃድ፣ ከ1 ሺህ 500 በላይ ሀሰተኛ ቪዛ እና ከአንድ ሺህ 800 በላይ የትውልደ ኢትዮጵያዊ መታወቂያን ያሰሩ ዜጎች በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች መገኘታቸውንም ዳይሬክተሯ ተናግረዋል።
በመሆኑም ህገወጥ ሰነድ ያለቸው ዜጎች ከጥር አንድ ቀን 2016 ዓ.ም እስከ ጥር 30 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ ባሉት 30 ቀናት ወደ ተቋሙ በመምጣት ህጋዊ ሰነድ እንዲዘጋጅ ጥያቄ እንዲያቀርቡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በሕገወጥ መልኩ በኢትዮጵያ የሚኖሩ እና የሌላ ሀገር ዜግነት ባላቸው አካላት ላይ በተጠቀሰው ጊዜ ህጋዊ ሰነድ እንዲዘጋጅላቸው ካለደረጉ መንግስት እርምጃ እንደሚወሰድም ወይዘሮ ሰላማዊት አሳስበዋል፡፡
ኢትዮጵያ የመዳረሻ ቪዛን ወይም ቪዛ ኦን አራይቫል አገልግሎትን ከመስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት ጀምሮ በመስጠት ላይ መሆኗ ይታወሳል።
የመዳረሻ ቪዛ እየተሰጣቸው ያሉት ከ120 ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ ለሚገቡ ጎብኚዎች ሲሆን ይህም አገልግሎቱን ፈጣን እና የጎብኚዎችን ቁጥር ለመጨመር በሚል ነው፡፡
በኢትዮጵያ ከ300 ሺህ በላይ ዜጎች ፓስፖርት እንዲሰጣቸው አመልክተው በመጠባበቅ ላይ የነበሩ ሲሆን ኪዚህ ውስጥ 110 ሺህ ያህል ዜጎች ፓስፖርት እንዳገኙ ዳይሬክተሯ ከዚህ በፊት በሰጡት መግለጫ ላይ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
አሁን ላይ ፓስፖርት እንዲያገኙ ለኢምግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ያመለከቱት ዜጎች ቁጥር 190 ሺህ እንደሆኑም ተገልጿል።
ተቋሙ ባለፉት ሶስት ወራት በሰራቸው ስራዎች ከ531 ሺህ በላይ ፓስፖርት ታትሞ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገባ ተደርጓል ያሉት ሀላፊዋ 43 ሺህ 366 ለሚሆኑ በአዲስ አበባ ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ፓስፖርት ተሰጥቷልም ብለዋል።
እንዲሁም 15 ሺህ 793 ለሆኑ ዜጎች ደግሞ ለአስቸኳይ ፓስፖርት ፈላጊዎች ሲሰጥ 8 ሺህ 500 ለሚሆኑ በክልሎች ለሚኖሩ ዜጎችም ፓስፖርት እንደተሰጡም ከአንድ ወር በፊት በነበረው መግለጫቸው ላይ ጠቅሰዋል።