ኢትዮጵያ በቀን ከ1 ሺህ 200 በላይ የቁም እንስሳት በሕገ-ወጥ መንገድ ከአገር በመውጣታቸው በየቀኑ ከ630 ሺህ ዶላር በላይ እንደምታጣ ተገልጿል።
በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ ገብተው ለአገልግሎት የሚወሉ መድኃኒቶችም የጥራት ደረጃቸውን ያልጠበቁ በመሆናቸው በጤና ሥርዓቱ ላይ ጫና እያሳደሩ መሆኑም ተገልጿል።
በኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አዘጋጅነት ሕገ-ወጥ ንግድን መከላከል ላይ ያተኮረ አገር አቀፍ ጉባዔ በአዲስ አበባ ዛሬ ተካሂዷል።
ምክር ቤቱ ሕገ-ወጥ ንግድ በስፋት በሚታይባቸው ዘርፎች ላይ ያካሄዳቸውን ጥናቶች ይፋ አድርጓል።
ጥናቶቹ በቁም እንስሳት፣ በመድኃኒት፣ በጨርቃጨርቅ፣ በሎጂስቲክስ ሥርዓት ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴዎችና ንግድን በተመለከቱ የሕግ ማዕቀፎች ላይ የተካሄዱ ናቸው።
አሁን ላይ የቁም እንስሳትና የመድኃኒት ሕገ-ወጥ ንግድ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ በጥናቱ ተመላክቷል።
በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኢንተርፕራይዝ ልማት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አለባቸው ንጉሴ፤ በቁም እንስሳት ኤክስፖርት ግብይት ላይ የሚታዩ ችግሮችና የመፍትሔ ሃሳቦችን በተመለከተ ጥናት አቅርበዋል።
በዚህም ባለፉት ስምንት ዓመታት ከቁም እንስሳት ንግድ የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ እየቀነሰ መምጣቱን ጠቅሰዋል፡፡
ለማሳያም ቀደም ሲል ከዘርፉ እስከ 150 ሚሊየን ዶላር የሚጠጋ ገቢ ይገኝ እንደነበር አስታውሰው፤ በ2014 ዓ.ም እና በ2015 ዓ.ም ገቢው ወደ 17 ሚሊየን ዶላር መቀነሱን አስረድተዋል።
የችግሩ ምንጭ የሕገ-ወጥ ንግድ ስልትና ዓይነት እየተቀያየረ መምጣቱ፣ የክትትልና የቁጥጥር ሥራው አጥጋቢ አለመሆን፣ በቴክኖሎጂ የተደገፈና ሕጉን የጠበቀ የግብይት ሥርዓትን ማስተግበር ላይ ክፍተቶች መኖራቸውን ጥናቱ አመላክቷል።
ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የቁም እንስሳት ልየታና ከተቀባይ አገራት ጋር ያለው ሕጋዊ ስምምነት ላይም ክፍተቶች እንደሚታዩ አንስተዋል።
በመሆኑም በቅርቡ በአገሪቱ በሦስት የመውጫ በሮች በተካሄደ ጥናት በቀን ከ1ሺህ 200 በላይ የቁም እንስሳቶች በሕገ-ወጥ መንገድ ከአገር እንደሚወጡ ተረጋግጧል ብለዋል።
በዚህም አንድ የቁም እንስሳት እስከ 530 ዶላር የሚያወጣ ሲሆን፤ አገሪቱ በቀን 630 ሺህ ዶላር በላይ በአንድ ወር ደግሞ 19 ሚሊየን ዶላር ታጣለች ሲሉ የችግሩን አሳሳቢነት አመላክተዋል።
የኢትዮጵያ የፋርማሲ ማኅበር ጠቅላላ ጉባዔ ምክትል ሰብሳቢ ዶክተር ወርቁ በዳዳ በበኩላቸው፤ በሕገ-ወጥ የመድኃኒትና የሕክምና መሳሪያ ንግድ ዙሪያ ጥናት አቅርበዋል።
ጥናት አቅራቢው በኢትዮጵያ በሕጋዊ መንገድ ሳይመዘገቡ አገልግሎት ላይ የሚወሉ፣ ከጥራት ደረጃ በታች የሆኑና የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው መድኃኒቶች ገበያ ላይ እንደሚውሉ ጠቁመዋል።
በወባ፣ በካንሰርና በሌሎች መድኃኒቶች ላይ የጥራትና የፈዋሽነት አቅም ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ አድርጓል ብለዋል።
ይህም ሕገ-ወጥ የመድኃኒት ግብይቱ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የሚያመለክት መሆኑንም አስረድተዋል።
በጉምሩክ ኮሚሽን የኢንተለጀንስ ዳይሬክተር ሰኚ ሰፋ፤ በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ያጋጠሙ የፀጥታ ችግሮች በመውጫ በሮች ላይ የሚደረገውን የቁጥጥር ሥራ እንዳዳከሙት ተናግረዋል።
ይህም ሕገ-ወጥ ንግዱ እንዲበራከትና ሕጋዊ የንግድ ሥርዓቱ እንዲዳከም በር መክፈቱን ጠቅሰዋል።
ይሁን እንጂ አስቻይ በሆኑ አካባቢዎችና ሁኔታዎች ላይ የቁጥጥር ሥርዓቱን በማጠናከር ችግሩን ለማቃለል ጥረት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ኢንጂነር መላኩ እዘዘው በበኩላቸው፤ በአሁኑ ወቅት በሁሉም ዘርፎች በሚባል ደረጃ ሕገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴው አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ተናግረዋል።
መንግሥት የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማጎልበት የተለያዩ የማሻሻያ ሥራዎችን ተግባራዊ እያደረገ ቢሆንም በሕገ-ወጥ ንግድ የሚሳተፋ ነጋዴዎችን ለይቶ ተጠያቂ ማድረግ ላይ ክፍተቶች መኖራቸውንም ጠቁመዋል።