በኢትዮጵያ ካሉ አልኮል አምራች ኩባንያዎች መካከል ዋነኛው የሆነው ቢጂአይ ኢትዮጵያ ስራ አስፈጻሚ ኤርቬ ሚላድ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ስራ አስፈጻሚው መግለጫ ከሰጡባቸው ጉዳዮች መካከል የድርጅቱ አዲስ እቅዶች፣ ዋና ቢሮውን ወደ ሰበታ ስለማዞሩ እና ማይጨው፣ ለፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ ስለተሸጠው ዋና መስሪያ ቤት ቦታ፣ ትርፍ እና ሌሎችም ጉዳዮች ዋነኞቹ ናቸው፡፡
ኤርቬ ሚላድ በመግለጫቸው ቢጂአይ ከዚህ ቀደም እራሳቸዉን ችለዉ አክሲዮን ማህበር ተብለዉ ሲጠሩ የነበሩት ኩባንያዎች ወደ ቢጂአይ ይዋሃዳሉ ብለዋል፡፡
ድርጅቱ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ውስጥ የቢራ ምርቱን አሁን ካለበት 5 ሚሊዮን ሄክቶሊትር ወደ 10 ሚሊዮን ሄክቶ ሊትር ማሳደግ የሚያስችሉ የምርት መሻሻያ ስራዎችን እንደሚሰራም ስራ አስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡
ከሚሰሩት ስራዎች መካከልም የቢራ ፋብሪካዎችን ምርታማነትን ማሳደግ፣ አዳዲስ ደንበኞችን እና አከፋፋዮችን መመልመል፣ የድርጅቱን ዋና መቀመጫ ከአዲስ አበባ ወደ ሰበታ መውሰድ፣ የስራ እና ሃላፊነት መደራረብን ማስቀረት፣ የራያ ቢራ እና ዘቢዳር ቢራ ፋብሪካዎችን ማስፋፋት ተጠቃሽ ናቸው፡፡
እንደ ስራ አስፈጻሚው ገለጻ አዲስ አበባ ሜክሲኮ ያለው የቢጂአይ ቢራ ዋና መቀመጫ ቢሮን ለፐርፐዝ ብላክ ተሸጧል፡፡
ድርጅቱ በመጪዎቹ 18 ወራት ውስጥ ቦታውን ሙሉ ለሙሉ ለፐርፐዝ ብላክ ያስረክባል ያሉት ስራ አስፈጻሚው በቀጣዮቹ ስድስት ወራት ውስጥ ደግሞ ድርጅቱ ወደ አዲሱ ቢሮው ያመራል ብለዋል፡፡
ላለፉት አስርት ዓመታት የቢጂአይ ዋና መቀመጫ ሆኖ ያገለገለውን ቢሮ እንድትሸጡ የመንግስት ተጽዕኖ ነበር? በሚል ከጋዜጠኞች ጥያቄ የቀረበላቸው የቢጂአይ ስራ አስፈጻሚ ኤርቬ ሚላድ “ቢጂአይ ቢሮውን የሸጠው ከፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ ጥሩ ክፍያ ስለቀረበለት እና ምን አልባት ወደፊት መንግስት ቢሯችሁን ከመሀል ከተማ ወደ ዳር አውጡ የሚል ጥያቄ ሊቀርብ ይችላል በሚል ስሌት እንጂ መንግስት ምንም አይነት ተጽዕኖ አላደረሰብንም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ስራ አስፈጻሚው አክለውም አሁን ላይ ቢጂአይ ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት የነበረውን የገበያ ድርሻ አጥቷል ያሉ ሲሆን የድርጅቱ የገበያ ድርሻ ሶስተኛ ደረጃ ላይ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
ከዲያጆ ኩባንያ የተገዙ የቢራ ፋብሪካዎች ከቢጂአይ ጋር ቢዋሃዱም ምርቶቻቸው ግን በነበሩበት ብራንድ ለገበያ መቅረባቸውን እንደሚቀጥሉም ስራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡
ከሰራተኞች ቅነሳ ጋር በተያያዘ ለተነሳላቸው ጥያቄም ድርጅቱ የሚገፋው ሰራተኛ ባይኖርም እድሜያቸው ለጡረታ የደረሱትን ተገቢውን ክፍያ ፈጽመን እናሰናብታለን፣ ተደራራቢ የሆኑ እና ምርታማ ያልሆኑ ሰራተኞችን ይዘን አንቀጥልም ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ በተለያዩ ቦታዎች ያለው ጦርነት እና የጸጥታ ችግሮች በቢጂአይ ኢትዮጵያ ላይ ምን አይነት ተጽዕኖ አደረሱ በሚል ለቀረቡ ጥያቄዎችም ስራ አስፈጻሚው በትግራይ የነበረው ጦርነትን ጨምሮ አሁን ያሉት አለመረጋጋቶች ድርጅቱ ምርቶቹን በፈለገው መንገድ ተዘዋውሮ እንዳይሸጥ፣ እንዳያንቀሳቅስ እና አከፋፋዮቹ ከስራ ውጪ እንዲሆኑ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የውጭ ምንዛሬ እጥረት እና የግብዓት እጥረቶች ድርጅቱን በየዕለቱ የሚያሳስቡ ጉዳይ መሆናቸውን የተናገሩት ስራ አስፈጻሚው ችግሮቹን ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንደሚነጋገሩም ጠቅሰዋል፡፡
ይሁንና በችግሮች መካከልም ቢሆን ቢጂአይ ኢትዮጵያ ትርፋማ መሆኑን እና በቀጣዮቹ ዓመታት ከነባሮቹ ምርቶች በተጨማሪ አዳዲስ ምርቶችን ለገበያ ሊያቀርብ እንደሚችልም ኤርቬ ሚላድ ተናግረዋል፡፡