በኢትዮጵያ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል እንዲወሰን ዓለም አቀፉ የሰራተኞች ድርጅት ጠየቀ

ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ማህበራዊ ፍትህ ለማስፈን በሚል ነበር ከ100 ዓመት በፊት ዓለም አቀፉ የሰራተኞች ድርጅት የተቀላቀለችው፡፡

ከአፍሪካ በብቸኝነት ድርጅቱን የተቀላቀለችው ኢትዮጵያ 100ኛ ዓመቱን በአዲስ አበባ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አመራሮች፣ አሰሪዎች፣ የሰራተኛ ማህበራት አመራሮች እና ባለሙያዎች በተገኙበት በማክበር ላይ ትገኛለች፡፡

በዚህ በዓል ላይ ተገኝነተው ንግግር ያደረጉት ዓለም አቀፉ የሰራተኞች ድርጅት የአፍሪካ ዳይሬክተር ፋፋን ርዋንይንዶ ካይራንግዋ እንዳሉት ኢትዮጵያ ከ23ቱ የአይኤልኦ ስምንቶች መካከል ስምንቱን ማጽደቋን አድንቀዋል፡፡

ዳይሬክተሯ አክለውም ኢትዮጵያ የሰራተኞችን ደህንነት ለማሻሻል በርካታ የወሰደቻቸው እርምጃዎች ቢኖሩም ለሰራተኞች የዝቅተኛ ደመወዝ እርከን ጣሪያን እንድትወስን ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሰማኮ) ፕሬዝዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ እንዳሉት ኢትዮጵያ ዓለም አቀፉን የሰራተኞች ድርጅት ከተቀላቀለች 100 ዓመት የሞላት ቢሆንም አሁንም ሰራተኞች መደራጀት ከማይችሉባቸው ጥቂት የአፍሪካ ሀገራት መካከል አንዷ ናት ብለዋል፡፡

በጦርነት ምክንያት ድርጅቶች እየወደሙ እና ሰራተኞችም አብረው ለከፋ ችግሮች እየተዳረጉ ነው ያሉት አቶ ካሳሁን በትግራይ በርካታ ድርጅቶች የዚህ ሰለባ እንደሆኑም ተናግረዋል፡፡

አቶ ካሳሁን አክለውም በአማራ ክልል ባለው ጦርነት ምክንያት ድርጅቶች ስራቸውን ማንቀሳቀስ እንዳልቻሉ ሰራተኞችም በዛው ልክ እየተገደሉ እና ለከፋ ችግር እየተዳረጉ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

እንዲሁም በኦሮሚያ በበርካታ ድርጅቶች ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች እየታገቱ እና እየተገደሉ ናቸው ያሉት አቶ ካሳሁን ጦርነት እና ግጭቶች እንዲቆሙ እና ችግሮች በውይይት ሊፈቱ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ለአብነትም በአንድ ወር ውስጥ እስከ 39 የአበባ እርሻ ልማት ሰራተኞች፣ የዳንጎቴ ሲሚንቶ እና ሙገር ሲሚንቶ ሰራተኞች በታጣቂዎች የተገደሉበት ወቅት እንደነበርም አቶ ካሳሁን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ቀድማ ዓለም አቀፉን የሰራተኞች ድርጅትን ብትቀላቀልም ስምምነቶችን እና አዋጆችን ከመተግበር አንጻር ወደኋላ የቀረች ሀገር ናትም ተብሏል፡፡

በተለይም ሰራተኞች ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ እንዲደራጁ የሚፈቅዱ ህጎች በኢትዮጵያ ቢኖሩም አሁንም ሰራተኞች መደራጀት እንዳይችሉ መከልከላቸውን አቶ ካሳሁን አንስተዋል፡፡

በኢትዮጵያ አራት ሚሊዮን ሰራተኞች እንዳሉ ቢገመትም የተደራጁት ግን አንድ ሚሊዮን እንኳን እንደማይሞላ የገለጹት አቶ ካሳሁን አብዛኛው ሰራተኞች የሚያገኙት ወርሃዊ ደመወዝ ምግብ በልተው ወደ ስራ እንዲገቡ የሚያደርግ እንዳልሆነም ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም መንግስት በተደጋጋሚ ለሚቀርብለት ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ጣሪያን የወስን ጥያቄ ምላሽ እንዲሰጥ ሲሉም አቶ ካሳሁን ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የስራ እና ክህሎት ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በበኩላቸው ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት በነበሩ መሪዎቿ አይኤልኦን ጨምሮ በርካታ ተቋማትን ከሌሎች ሀገራት ጋር በመሆን መመስረቷን ተናግረዋል፡፡

አባቶቻችን ላደረጉት ጥረት ምስጋና ይገባቸዋል ያሉት ሚኒስትሯ የኢትዮጵያ አሻራ ያለበት አይኤልኦ በዓለም ካሉ ስኬታማ ተቋማት መካከል አንዱ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

ሚኒስትሯ አክለውም መንግስት ባለፉት አምስት ዓመታት ማህበራዊ ፍትህን እና የሰራተኞች ደህንነትን ለማረጋገጥ ስር ነቀል ለውጥ ለማምጣት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሰፊ የስራ እድል የሚፈጥሩ የስራ ክፍሎች እና ለግል አሰሪ ተቋማት የገንዘብ እጥረት እንዳይገጥማቸው በየዓመቱ ሰፊ የብድር አቅርቦት በመቅረብ ላይ መሆኑንም ሚኒስትሯ ገልጸዋል፡፡

ሚኒስትር ሙፈሪያት አክለውም መንግሥት ሰራተኛው ላይ ያለውን ጫና ይረዳል፣ በዚህ ረገድ መሰረታዊ ለውጥ እንዲመጣ እየሰራን ነው። ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ለመወሰን ጥናት በመደረግ ላይ ነው፣ በቅርቡ ይጠናቀቃል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *