የፈረንሳዩ ኩባንያ የኢትዮ ቴሌኮምን ድርሻ ለመግዛት የጀመረውን ጥረት እቅድ ሰረዘ

ኦሬንጅ የተሰኘው የፈረንሳይ የቴሌኮም ኩባንያ ከኢትዮቴሌኮም 45 በመቶ አካባቢ ድርሻ ለመግዛት ዕቅድ የነበረው ቢሆንም ኃሳባችንን በፍጥነት ለመተግበር እና ውጤት ለማግኘት የሚያስችል ሁኔታ ባለመኖሩ ራሴን አግልያለሁ ብሏል።

ኢትዮጵያ ከመንግስታዊው ኢትዮቴሌኮም እና በቅርቡ ገበያውን ከተቀላቀለው ከሳፋሪኮም በተጨማሪ ሦስተኛ የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢ ስራ እንዲጀምር ፈቃድ ለመስጠት ገበያውን እየገመገመ የቆየች ሲሆን በቅርቡ የገበያው ሁኔታ የታሰበውን ያህል አመርቂ ባለመሆኑ ሐደቱ ተቋርጧል ማለቷ ይታወሳል።

ከዚህ ጎን ለጎን ከኢትዮቴሌኮም ከግማሽ ያነሰ ድርሻ ለመሸጥም እየጣረች ሲሆን ኦሬንጅ ድርሻ ለመግዛት ፍላጎት ካሳዩት ዓለምአቀፍ ግዙፍ ኩባንያዎች መካከል አንዱ ነበር።

ኩባንያው ሞባይል ለዎርልድ ላይቭ እንደገለፀው ከ2021 ጀምሮ የነበረውን ፍላጎት አሁን መግታቱን ይፋ አድርጓል።

ኦሬንጅ ግሩፕ በጉዳዩ ላይ ትንተና ከሠራ በኋላ “ስትራቴጂያችንን በፍጥነት ለመተግበር እንዲሁም ለኩባንያችን እሴትን በሚያስገኝ መልኩ ፕሮጄክቱን ለማጠናቀቅ የሚያስችሉ ሁኔታዎች እንደሌሉ አምነናል” ብሏል።

ከኦሬንጅ በተጨማሪ መቀመጫውን በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ያደረገው ኢ& (ኢ ኤንድ) ኩባንያ ፍላጎት አሳይቷል ተብሏል።

ኦሬንጅ ኢትዮጵያ ከሁለት ዓመት በፊት ከመንግስታዊው የቴሌኮም ተቋም ድርሻ ለመሸጥ የጨረታ ሒደት ይፋ ስታደርግ ፍላጎቱን አሳውቆ የነበረ ቢሆንም መንግስት ከአንድ ዓመት በኋላ የሽያጭ ሒደቱን እንዳቋረጠ ይፋ አድርጓል። ከቆይታ በኋላ ሒደቱ ዳግም ተከፍቷል።

በጦርነት እና በግጭቶች ምክንያት ምጣኔ ኃብቷ የተጎሳቆለው እና የውጭ ኢንቨስትመት መሳብ ያዳገታት ኢትዮጵያ ገበያዋን ለመከፈት ጥረት እያደረገች ትገኛለች።

የብሔራዊው ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ ከሰሞኑ የባንክ ዘርፉን ለውጭ ተፎካካሪዎች ክፍት ለማድረግ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ማሞ ዘ ባንከር ከተባለ በዘርፉ ዙርያ ከሚያጠነጥን እና መቀመጫውን በእንግሊዝ ካደረገ መፅሔት ጋር ባደረጉት ቆይታ ኢትዮጵያ ምርትን ወደውጭ በመላክ ላይ ያተኮሩ ኩባንያዎችን እንዲሁም የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ማነቆ የሆኑ መመሪያዎችን እያላላች መሆኑን ተናግረዋል።

ማሞ ጨምረውም ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር ተከታታይ ውይይቶችን እያደረጉ እንደሆነ ገልፀዋል። ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት አይኤምኤፍ ጋር የኢትዮጵያን የውጭ ምንዛሬ ክምችት ለማሳደግ የሚያግዙ ስምምነቶች ላይ ለመድረስ ተስፋ እንዳላቸውም አክለው ተናግረዋል።

ከሁለት ዓመት በፊት በዓለም አቀፍ ጨረታ አማካኝነት የኢትዮጵያን ቴሌኮም ገበያ የተቀላቀለው ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ከ4 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች ማፍራቱን ከሰሞኑ መግለጹ ይታወሳል፡፡

ይሁንና በኢትዮጵያ ያለው የጸጥታ ሁኔታ እና የኑሮ ውደነቱ ለስራው እንቅፋት እንደፈጠረበት የገለጸ ሲሆን ከ2 ዓመት በላይ በጦርነት ውስጥ ወደ ቆየችው ትግራይ ክልል የቴሌኮም አገልግሎት ለመጀመር በጥረት ላይ መሆኑንም አስታውቋል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *