የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ሰራተኞች ህዝብን ከማማረራቸው ባለፈ ለውጭ ሀገራት ዜጎች ፓስፖርት ሲሰጡ ነበርም ተብሏል፡፡
በሙስና ተጠርጥረው በፖሊስ ከታሰሩ ሰዎች መካከል የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተሩ ይገኙበታል፡፡
42 የኢምግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ሰራተኞች ባሳለፍነው ሰኞ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በህግ ቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
የመንግሥት አስተዳደር ለውጥ ከተደረገ ጀምሮ የኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ አገልግሎት ተቋም ውስጥ የተለያዩ ለውጦች (ሪፎርም) የተደረገ ቢሆንም፣ አንዳንድ የተቋሙ ሠራተኞች በድለላ ሥራ የተሰማሩ አካላት ጋር በመመሳጠር የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው በቁጥጥር ሥር ውለው በምርመራ ላይ ናቸው ተብሏል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ባሳለፍነው ሀምሌ ወር ላይ ፓስፖርት ፈላጊ ኢትዮጵያዊያን መንገላታታቸውን ተከትሎ የተቋሙን አመራሮች ከስልጣን አግደው ነበር፡፡
ሰላማዊት ዳዊት ደግሞ የኢምግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎትን በዋና ዳይሬክተርነት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሾሙ ሲሆን አሁን ላይ ተቋሙ የተሻለ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ከተጠርጣሪዎቹ መካከልም ሁለት ደላሎች ሌሎች ሁለት በወንጀሉ ተሳትፈዋል የተባሉ የውጭ ሀገር ዜጎች ይገኙበታል።
ቀሪዎቹ ተጠርጣሪዎች ደግሞ የኢትዮጵያ ኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ አገልግሎት ሰራተኞች ናቸው ተብሏል።
ተጠርጣሪዎቹ ከግለሰብና ከደላላ ጋር በጥቅም በመመሳጠር፣ ከህግ ውጪ ለውጭ ሀገር ዜጎች ከ10 ሺህ ብር እስከ 300 ሺህ ብር በሚደርስ ጉቦ በመቀበል ፓስፖርት በመስጠት እና በህጋዊ መንገድ የተመዘገቡ ተገልጋዮችን በማጉላላት በሀገር ጥቅም ላይ ጉዳት በማድረስ ሙስና ወንጀል ጠርጥረዋል።