ባሳለፍነው ሐምሌ ወር ላይ በሱዳን ለተከሰተው ጦርነት እልባት ለመፈለግ በሚል በካይሮ በተካሄደው የጎረቤት ሀገራት መድረክ ላይ ለመሳተፍ ወደ ስፍራው ያቀኑት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ጋር የህዳሴው ግድብ የሶስትዮሽ ድርድርን ለማስቀጠል መስማማታቸው ተገልጾ ነበር፡፡
በዚህ ስምምነት መሰረት ከሶስት ሳምንት በፊት የኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን የግድቡ ተደራዳሪ የቴክኒክ ባለሙያዎች በግብጽ ካይሮ ተገናኝተው ተወያይተዋል።
እንዲሁም ሁለተኛው ዙር የቴክኒክ ባለሙያዎች ውይይት ደግሞ ባሳለፍነው ቅዳሜ እና እሁድ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
የኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን የግድቡ ተደራዳሪዎች፣ ባለሙያዎች እና ዲፕሎማቶች የተሳተፉበት ይህ ውይይት ከተጠናቀቀ በኋላ የሁለቱም ሀገራት በጉዳዩ ዙሪያ መግለጫ አውጥተዋል፡፡
የግብጽ ውሃ እና መስኖ ሚኒስትር ሀኒ ስዌለም እንዳሉት በአዲስ አበባ የተካሄደው ድርድር ያለ ስምምነት መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡
እንደ ኢጅፕት ኢንዲፐንደንት ዘገባ ከሆነ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ የተናጠል ውሳኔዎችን በመወሰን የግድቡን ውሃ መሙላቷን የተቃወሙ ሲሆን የተናጠል ውሳኔዎች የሶስትዮሽ ድርድሩን ይጎደዋል ብለዋል፡፡
ይሁንና ግብጽ አሁንም በቅኝ ግዛት ዘመን የነበሩ ስምምነቶች እንዲከበሩ መጠየቋ እንዳሳዘነው የገለጸው የኢትዮጵያ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በ2015 በተደረሰው የመርሆች ስምምነት መሰረት በታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ላይ ጉልህ ጉዳት በማያደርስ መንገድ ወደ ስምምነት መምጣት እንዲቻል ጥረቷን እንደምትቀጥል አስታውቋል፡፡
በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ተደራዳሪዎች መካከል አንዱ የሆኑት አምባሳደር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) በበኩላቸው በአዲስ አበባ የተካሄደው ሁለተኛው የሶትዮሽ ውይይት በስኬት መጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ አራተኛው ዙር የህዳሴውን ግድብ የውሃ ሙሌት ማጠናቀቋ ይታወሳል፡፡
በሀይል የማመንጨት አቅሙ ከአፍሪካ አንደኛ የሆነው ይህ ግድብ እስካሁን ከ180 በላይ ቢሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት ሲሆን ቀሪ ግንባታውን ለማጠናቀቅ 60 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።
የህዳሴው ግድብ ከሁለት ዓመት በኋላ ሙሉ ለሙሉ ይጠናቀቃል የተባለ ሲሆን አሁን ላይ ከ40 ቢሊዮን በላይ ሜትር ኪዩብ ውሀ በግድቡ ውስጥ ይገኛል ተብሏል።