የታላቁ ህዳሴ ግድብ አምስት ተርባይኖች በቅርቡ ሀይል ማመንጨት እንደሚጀምሩ ተገለጸ

በ2016 በሕዳሴው ግድብ አምስት ተጨማሪ ዩኒቶችን ሥራ ለማስጀመር እየተሠራ መሆኑን፤ የታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ አስታውቀዋል፡፡

የሕዳሴ ግድቡ አራተኛ ዙር የውኃ ሙሌት መጠናቀቁን ተከትሎ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት የሙሌቱ መጠናቀቅ በይፋ ተበስሯል፡፡

በሥፍራው ለተገኙ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ማብራሪያ የሰጡት የታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ፤ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ 93 በመቶ መጠናቀቁን መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ግድቡ፤ ግራ፣ ቀኝ እና መካከለኛ አካል እንዳለው የተናገሩት ኢንጂነር ክፍሌ፤ ግራና ቀኙ የግድቡ ክፍል ከ635 እስከ 645 ደረጃ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡

የግራና ቀኙን ክፍል ለማጠናቀቅ ከዘጠኝ እስከ አሥር ሜትር ድረስ ብቻ እንደሚያስፈልግም አስታውቀዋል፡፡

የግድቡን መካከለኛ ክፍል ለማጠናቀቅ ደግሞ 20 ሜትር እንደሚቀር የገለጹ ሲሆን፤ ከአንድ ዓመት በኋላ የግድቡ መካከለኛው ክፍል እንደሚጠናቀቅ አስታውቀዋል፡፡

አክለውም የሚቀረው ሥራ ግራና ቀኙን የግድቡን ክፍል የሚያገናኝ ድልድይ መሥራት መሆኑንም በማንሳት፤ ከአራት ወር በኋላ የግድቡ ግራና ቀኝ ክፍል 645 ላይ ይደርሳል ተብሏል።

በግድቡ ኤሌክትሮ መካኒካል ተከላዎች እየተካሄዱ መሆናቸውን ያስታወቁት ኢንጂነር ክፍሌ፤ ግድቡ አሁን ላይ በኹለት ዩኒቶች እያመነጨ እንደሚገኝና በ2016 ተጨማሪ አምስት ዩኒቶች ሀይል ማመንጨት እንደሚጀምሩ ገልጸዋል፡፡

በሀይል ማመንጨት ከአፍሪካ ትልቁ ግድብ የሆነው የሕዳሴው ግድብ በአጠቃላይ ሀይል የሚያመነጩ ሰባት ዩኒቶች ይኖሩታል ተብሏል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *