ኢትዮጵያ የሲንጋፖር ኩባንያን ወደ ሀገሯ እንዲመጣ ጋበዘች

የሲንጋፖር የወደብ ባለስልጣን በኢትዮጵያ በሎጀስቲክስ ኢንቨስትመንት እንዲሰማራ ጥሪ ቀረበ

ዓለም አቀፍ የእስያ ኩባንያዎችን ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ እና ኢንቨስት እንዲያደርጉ ለማሳመን የኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ሲንጋፖርን በመጎብኘት ላይ ናቸው፡፡

የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ ጋር በመሆን ሲንጋፖር የሚገኘውን የሲንጋፖር የወደብ ባለስልጣን ጎብኝተዋል።

ሁለቱ የኢንቨስትመንት አመራሮች ከሲንጋፖር ወደብ ባለስልጣን ኃላፊዎች ጋር ውይይት አድርገዋል።

በውይይቱም የሲንጋፖር የወደብ ባለስልጣን በኢትዮጵያ በሎጀስቲክስ ኢንቨስትመንት እንዲሰማራ ጠይቀዋል።

የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜ፣ ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን ከፍተኛ ፍላጎት ገልፀው ባለስልጣኑ በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት የሚሰማራበትንና ልምድ የሚያካፍልበት መንገድ እንዲኖር ጥሪ አቅርበዋል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ በበኩላቸው ፈጣን ፤ ቀልጣፋና ውጤታማ የሎጀስቲክስ አገልግሎት መኖር ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፍና ለኢንዱስትሪ ልማት ግብዓት የሚሆኑ ጥሬ እቃዎች አቅርቦትና ኤክፖርት ላይ የሚኖረው ፋይዳ ጉልህ መሆኑን ገልፀው ለዘርፉ እድገትም የማይተካ ሚና እንደሚኖረው ጠቁመዋል።

የሲንጋፖር የወደብ ባለስልጣን ከ50 ዓመታት በላይ ልምድ ያለውና ከ200 ሺህ በላይ ግዙፍ ኮንቴነሮችን በአንድ ግዜ ማስተናገድ የሚችል ወደብን ያስተዳድራል ተብሏል፡፡

እንዲሁም  በኮንቴነር ማስተናገድ አቅሙ ከአለም ቁጥር አንድ ሲሆን ወደቡ ቀልጣፋ የሎጀስቲክስ ስራዎችን እያከናወነም ይገኛል።

ኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ከአፍሪካ ቀዳሚ ሀገራት መካከል አንዷ የነበረች ቢሆንም ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ በጦርነት ውስጥ መቆየቷ ጎድቷታል፡፡

በተለይም አሜሪካ ኢትዮጵያን ለአፍሪካ ሀገራት ከሰጠችው ከቀረጥ ነጻ ምርቶችን ወደ አሜሪካ ገበያዎች እንዲያስገቡ የሚፈቅደው ወይም አግዋ እድልን ማገዷ ከጉዳቶቹ መካከል ዋነኛው ነው፡፡

በኢትዮጵያ ተሰማርተው የነበሩ በርካታ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ኢትዮጵያ ከአግዋ እድል በመሰረዟ ምክንያት የለቀቁ ሲሆን የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰትም ቀንሷል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *