እስራኤል ከአማራ ክልል 200 የሚሆኑ ዜጎቿንና አይሁዳውያንን ማስወጣቷን አስታወቀች።
የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚንስቴርና የጠቅላይ ሚንስቴር ጽ/ቤት በጋራ ባወጡት መግለጫ በክልሉ በተነሳው ግጭት 174 እስራኤላዊያንና ወደ ሀገሪቱ ለመግባት ብቁ የሆኑ ቤተ-እስራኤላዊያን ከጎንደር እንዲወጡ ተደርጓል።
ሌሎች 30 የሚሆኑ ዜጎች ደግሞ ከባህር ዳር መውጣታቸው ተነግሯል።
በአራት በረራዎች ከአማራ ክልል እንዲወጡ የተደረጉት ዜጎች አዲስ አበባ ደርሰዋል ተብሏል። ከአዲስ አበባም ወደ እስራኤል ያቀናሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ኢላይ ኮን እስራኤላዊያኑ ወደ ሀገራቸው ለመመለስ እስኪወስኑ ድረስ በአዲስ አበባ እንደሚቆዩ ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ መቆየትም እንደሚችሉም ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ እስራኤል ዜጎቿን የትም ይሁኑ የት ጥበቃ እንደምታደርግላቸው መናገራቸውን የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኸን ዘግቧል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ “አጭር፣ ኮሽታ ያልተሰማበትና ውጤታማ” ላሉት ተልዕኮ ለተሳተፉ አካላት ምስጋና ችረዋል።
የፌደራል መንግስት ባለፈው ሚያዚያ ወር የክልል ልዩ ኃይሎችን ለማፍረስና መልሶ ለማደረጃት መወሰኑን ተከትሎ በአማራ ክልል ያለው የጸጥታ ችግር እየተባባሰ መጥቷል።
መንግስት ስድስት የአማራ ክልል ከተሞችን ከታጣቂዎች ስጋት ነጻ ማድረጉን እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መጣሉንም አስታውቋል።