ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ካቢኔያቸውን በትነው ስልጣን እንዲለቁ ተጠየቁ

ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥያቄዎች በመቀበል ላይ ናቸው።

የባህርዳር ህዝብን ወክለው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያሉት ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) ለጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ጥያቄ አቅርበዋል።

የአብን ተወካዩ እንዳሉት
“ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደስልጣን ከመጡ ወዲህ ኢኮኖሚዉ ታሟል፣ ወጣቶች ሀገራቸዉ ዉስጥ ተስፋ በማጣታቸው ስደትን ምርጫቸዉ አድርገዋል” ብለዋል።

“ዜጎች በጠራራ ፀሀይ ይታገታሉ ፣ ብልጽግና መራሹ ፓርቲ ሀገሪቱ ከገባችበት ቅርቃር ማዉጣት አልቻለም” ያሉት የምክር ቤቱ አባሉ ስልጣኖን ለጊዜያዊ አስተዳደር እንዲያስረክቡ ሲሉ ጠቅላይ ሚንስትሩን ጠይቀዋል።

ሌላኛው የምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ አዳነ ተሾመ በበኩላቸው ” ዜጎችን በማገት በሚሊዮን ገንዘብ መጠየቅ የዜጎችን ሰላም ወጥቶ መግባት ጥያቄ ዉስጥ ከትቶታል።

በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ያሉ ችግሮች በዘላቂነት እንዲፈቱና የህዝቡን ሰላም ለማስጠበቅ ምን እየተሰራ ይገኛል?

ልዩ ሀይሎችን ትጥቅ አስፈትቶ መልሶ ማደራጀት ላይ በተለይም በአማራ ክልል የተፈጠረዉን ችግር መንስኤዉን ለይቶ ለመፍታት ምን ታስቧል? እንደ ሀገርስ በሁሉም ክልሎች ያለዉ የመልሶ ማደራጀት ስራዉ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?” በሚል ጠይቀዋል።

ሌላኛው የምክር ቤቱ አባል አቶ መሀመድ አህመድ  ” ህወሓት አሁንም ከዉድቀቱ ያልተማረ መሆኑ እና ዛሬም የትግራይ ክልልን እና መላዉ ኢትዮጵያን መልሶ ጦርነት ዉስጥ ለመክተት እየተንቀሳቀሰ እንዳለ አሁንም ይነሳል። ወቅታዊ የትግራይ ክልል ሁኔታ ማብራሪያ ቢሰጥበት?” ሲሉ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅርበዋል።

ሌሎችም የምክር ቤቱ አባላት ጥያቄዎችን በማቅረብ ላይ ሲሆኑ ጠቅላይ ሚንስትሩ ቆይተው ምላሽ እንደሚሰጡባቸው ይጠበቃል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *