ደቡብ ኮሪያ በኢትዮጵያ ግብርናን ለማዘመን 10 ሚሊዮን ዶላር ለገሰች

ኢትዮጵያ እና የኮሪያ ዓለም አቀፍ የትብብር ኤጀንሲ የ10 ሚሊየን ዶላር የድጋፍ ስምምነትን በአዲስ አበባ ተፈራርመዋል።

የገንዘብ ድጋፍ ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው እና በኢትዮጵያ የኮይካ ሃላፊ ሊ ቢዩንግህዋ ፈርመውታል።

የገንዘብ ድጋፉ የኢትዮጵያን ግብርና ለማዘመን ይውላል የተባለ ሲሆን በተለይም የወተት እና የወተት ተዋጽኦ ምርታማነትን ለማሳደግ ያስችላል ተብሏል።

የወተት ምርታማነትን የሚያሳድገው ይህ ፕሮጀክት በቀጣዮቹ ስድስት ዓመታት እንደሚተገበር የገንዘብ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ፕሮጄክቱ በወተት ልማት እና እንስሳት እርባታ ዘርፍ የተሰማሩ አርሶ አደሮችን መደገፍ ላይ ትኩረቱን እንደሚያደርግም ተገልጿል።

የተሻሻሉ የወተት ላሞችን ለአርሶ አደሩ ማቅረብ፣ የወተት ምርታማነትን መጨመር፣ በማህበር የተደራጁ ወተት አቅራቢዎችን የገበያ እድሎችን ማስፋት፣ ተጨማሪ ሌሎች አሰራሮችን መዘርጋት የፕሮጀክቱ ዓላማ ነው ተብሏል።

ኢትዮጵያ በቀንድ ከብቶች ብዛት ከአፍሪካ አንደኛ ከዓለም ደግሞ 10ኛ ብትሆንም የአንድ ኢትዮጵያዊ አመታዊ የወተት ፍጆታ ግን ከ10 ሊትር በታች እንደሆነ ከዚህ በፊት የተደረጉ ጥናቶች ያሳያሉ።

የወተት ፍጆታ ማነስን ተከትሎም በኢትዮጵያ በምግብ እጥረት የቀነጨሩ ህጻናት ካሉባቸው የዓለማችን ሀገራት መካከል ዋነኛዋ አድርጎታል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *