በአዲስ አበባ አንድ የወረዳ አመራር በፖሊስ ተገደሉ
በአዲስ አበባ ከተማ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 08 ዋና ስራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ አለባቸው አሞኜ በቢሯቸው ውስጥ በአዲስ አበባ ፖሊስ አባል ተገደሉ።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ባወጣው መግለጫ ግድያውን የፈፀመው በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የካሳንቺስ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት የቀጠና ኦፊሰር የሆነ አባል ነው፡፡
የፖሊስ አባሉ የግል ጉዳዩ እንዲፈፀምለት በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ለወረዳ 8 አስተዳደር ጽ/ቤት ያመለከተውን ማመልከቻ ለመከታተል ወደ ወረዳው መጽህፈት ቤት መሄዱን ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡
የወረዳው ስራ አስፈጻሚም ጉዳዩን ተመልክቶ ምላሽ እንደሚሰጠው የተገለፀለት ቢሆንም ጥያቄዬ እንዳይፈፀም የከለከልከው አንተነህ በሚል ምክንያት ቢሯቸው ውስጥ በስራ ላይ እንዳሉ በታጠቀው ሽጉጥ መግደሉን ኮሚሽኑ በመግለጫው ላይ ጠቅሷል፡፡
ወንጀሉን የፈፀመው የፖሊስ አባል በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራው እየተጣራ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል።