የመንግስት ኮሙንኬሽን ጉዳዮች ሚንስቴር ባወጣው መግለጫ በኦሮሚያ ክልል ያለውን ግጭት በማስወገድ ሰላምን ለማምጣት ያለመውና በታንዛኒያ ሲካሄድ የቆየው የሰላም ውይይት የመጀመሪያ ምዕራፍ ተጠናቋል ብሏል።
ውይይቱ በአብዛኛው በአዎንታዊ መልኩ የተከናወነ ነው ያለው ሚንስቴሩ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ግን በዚህኛው የውይይት ምዕራፍ ስምምነት ላይ አልተደረሰም ብሏል።
ግጭቱን በዘላቂነትና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለማስቆም እንዲቻል ሁለቱም አካላት የሰላም ውይይቱን መቀጠል አስፈላጊ መሆኑ ላይ እንደተግባቡ ተገልጿል።
በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትና እስካሁን ሲመራባቸው በነበሩ መሠረታዊ መርሖች መሠረት ግጭቱን በሰላማዊ መልኩ ለመፍታት መንግስት የጸና አቋም እንዳለው በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።
ይህንን መልካም አጋጣሚና በውይይት ችግሮችን የመፍታት በጎ ጅምር በመጠቀም ጉዳዩ እልባት እንዲያገኝ የኢትዮጵያ መንግሥት ፅኑ አቋም እንዳለው አስታውቋል።
አሜሪካ በታንዛኒያ ራስ ገዝ አስተዳድር በሆነችው ዛንዚባር እየተካሄደ ያለው ድርድርን በአወንታዊ መልኩ እንደምትመለከተው መግለጿ ይታወሳል።
የአውሮፓ ህብረት በበኩሉ ክበሰሜን ኢትዮጵያ ተከስቶ በነበረው ጦርነት ሻክሮ የነበረው ግንኙነቱ ወደ ቀድሞ ሁኔታው እንዲመለስ መወሰኑን ከሰሞኑ አስታውቋል።
ይሁንና በኦሮሚያ እና አማራ ክልልሎች ያሉት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና አለመረጋጋቶች እንደሚያሳስቡት ገልጿል።