የከፊ ሚኒራልስ ኩባንያ አካል የሆነው ቱሉ ካፒ ጎልድ ማይኒንግ ከእንግሊዙ ‘PW ማይኒንግ’ ጋር የወርቅ ማዕድን ልማትና በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ አብሮ ለመስራት ስምምነት ተፈራርሟል።
ስምምነቱ የተፈረመው ከትናንት ሚያዚያ 18/2015 ጀምሮ በአዲስ አበባ ስካይላይት ሆቴል በመካሄድ ላይ በሚገኘው፤ “ኢንቨስት ኢትዮጵያ 2023” ዓለም አቀፍ የንግድ ተቋማትና ባለሃብቶች ፎረም ጎን ለጎን ነው።
በፎረሙ ከዓለም ዙሪያ የተውጣጡ ባለሃብቶች፣ የንግድ ተዋንያን፣ ፖሊሲ አውጪዎች እና ሥራ ፈጣሪዎች እየተሳተፉበት የሚገኝ ሲሆን፤ በመድረኩ የመግባቢያ ሰነድ ስምምነቶች፣ የፓናል ውይይቶች፣ የተመረጡ ኩባንያዎች ጉብኝትና አውደ ርዕይዎች እየተከናወኑ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ኢንቨትመንት ኮሚሽን አዘጋጅነት የሚከናወነው ይህ ፎረም በግብርና፣ ማንፋክቸሪንግ፣ አይ.ሲ.ቲ፣ ማዕድን እና በቱሪዝም ላይ ትኩረቱን አድርጓል።
በፎረሙ ላይ የኢትዮጵያ ኢንቨሰትመንት ኮሚሽነር ለሊሴ ነሜ፣ ዓለም አቀፍ ባለሃብቶች ፣ ዲፕሎማቶች፣ የልማት አጋሮችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተውበታል።
በዛሬው ዕለት የተከናወነው የፊርማ ስምምነትም የዚሁ የኢንቨስትመንት ፎረም አንዱ አካል ሲሆን፤ ስምምነቱ በቱሉ ካፒ ጎልድ ማይኒንግ ካንትሪ ዳይሬክተር አበራ ማሞ፣ በየከፊ ሚኒራልስ ኩባንያ ሊቀመንበር ሄሪ አናጎኖስትራራስ አደምስ፣ በPW ማይኒንግ ፋይናንስ ዳይሬክተር ሲራን ኩዊን እንዲሁም በኢትዮጵያ የብሪታንያ እና የአውስትራሊያ ተወካዮች መካከል ተከናውኗል።
ስምምነቱ ቱሉ ካፒ የተያዘውን የወርቅ ማዕድን ልማት ፕሮጀክት በዘመናዊ መንገድ ለማከናወንና በፋይናንስ ለመደገፍ ታስቦ የተከናወነ ሲሆን፤ ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ የሚሆን 400 ሚሊዮን ዶላር ተመድቧል።
ፕሮጀክቱ ተግባራዊ ሲደረግም የማዕድን ልማት ሥራን ያዘምናል የተባለ ሲሆን፤ ከ5 እስከ 10 ሺሕ ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ተገልጿል።
ነገ ሚያዚያ 20/2015 የሚያበቃው “ኢንቨስት ኢትዮጵያ 2023” ፎረም፤ “በኢትዮጵያ ኢንቨስት በማድረግ በልፅጉ – ማራኪ የኢንቨስትመንት አማራጮች ያሏት ምድር” በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
ፎረሙ በኢትዮጵያ ያሉትንና ያልተነኩ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለዓለም ለማስተዋወቅ ምቹ አጋጣሚ እንደሚፈጥር የተገለጸ ሲሆን፤ መርሐ-ግብሩን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ኢትዮ ቴሌኮም ዋና አጋር በመሆን ሲያዘጋጁት ፥ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበኩሉ የፎረሙ ሕጋዊ የጉዞ አጋር መሆኑ ተመላክቷል፡፡