ኢትዮጵያ በግብጽ ጫና ምክንያት ከ22 በላይ ፕሮጀክቶችን ማቋረጧ ተገለጸ

ኢትዮጵያ በየዘመናቱ በግብጽ ጫና ምክንያት በትንሹ 22 ፕሮጀክቶችን ለመሠረዝ አልያም በመከልከሏ ምክንያት ሳይሠሩ ለመቅረት መገደዳቸውን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ጋር በቀጣናዊና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ባደረጉት ቆይታ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ፕሮጀክቶቹን መሥሪያ ገንዘብ ከማጣቷ ባለፈ ፕሮጀክቶቹ በታሰቡት ወቅት ተሠርተው ቢሆን ኖሮ ሀገሪቱ ያጋጠማትን ድርቅና የጠፋውን የሰው ሕይወት መታደግ ይቻል እንደነበር ገልጸዋል።

የብሔራዊ የጉዳትና የካሳ ኮሚቴ አሁናዊ ሁኔታን በሚመለከት ምላሽ የሰጡት ዶ/ር ሀብታሙ፤ ኮሚቴው የሕግ ጉዳይ የሚያውቁ ባለሙያዎችን ያካተተና ዓለም አቀፍ ተሞክሮን መሠረት በማድረግ የሚሠራ መሆኑን ተናግረዋል። ጉዳዩ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተለያዩ ተቋማትን የሚመለከት በመሆኑ ከተቋማቱ ጋር በመነጋገር በቅርቡ ዝርዝሩ ይፋ እንደሚደረግም አስታውቀዋል።

ግብጽ ፕሮጀክቶቹ እንዳይሠሩ ለሠራችው የሎቢ (የማግባባት) ሥራ በእርግጠኝነት የምትከፍለው ዋጋ ይኖራል ያሉት ሚኒስትሩ፤ እንዴት ትከፍላለች? የሚለው ግን በሂደት የሚታይ ጉዳይ መሆኑን ጠቁመዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እንዲሠራ ሊያግዙን የነበሩ ብዙ አካላት ቢኖሩም፣ ግብጽ ድጋፍ እንዳይደረግ ከማድረጓ ባለፈ ግንባታው እንዲቆምና የብዙ ዜጎች ደም እንዲፈስ አድርጋለች ብለዋል። ይህንን ሁሉ ጨምሮ ምላሽ የሚሰጠው ኮሚቴ በሚያከናውነው ሥራ ለግብጽ ጥሩ ትምህርት የሚሰጥ ውጤት እንደሚገኝ እምነት መኖሩን ተናግረዋል።

በቅርቡ ግብጽና ሱዳን በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቻቸውና በውሃ ሚኒስትሮቻቸው በኩል እ.ኤ.አ. በ1959 ዓባይን በብቸኝነት ለመቆጣጠር ያደረጉትን የቅኝ ግዛት ዘመን ስምምነት ማደሳቸውን በሚመለከት ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ድርጊቱ ውጤት የማያመጣና የግብጽን መደናበር የሚያሳይ ነው ብለዋል።

እንዲሁም የሱዳን ወታደራዊ መንግሥት ከግብጽ ጋር የሚያደርገው ትብብር የሱዳንን ብሔራዊ ጥቅም የሚጎዳና የአስዋን ግድብን በመገንባት ሕዝባቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት ካደረሰ ሀገር ጋር የሚደረግ ትብብር ነው ሲሉ ሚኒስትሩ ገልጸውታል።

ኢትዮጵያ የሱዳን ሰላም እንዲጠበቅ ከማድረግ ባለፈ፣ ከሀገሪቱ በሚፈሰው ውሃ በመስኖ እንዲጠቀሙ ማድረግና በሁለቱ ሀገራት ላይ ያሉትን ግድቦች በመንገድ በማስተሳሰር ለቱሪዝም በር በመክፈት የጋራ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥን ጨምሮ ብዙ መሠራት የሚችሉ ሥራዎች መኖራቸውን አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ እና ግብጽ በአባይ ወይም ናይል ወንዝ አጠቃቀም ጉዳይ አለመግባባት ውስጥ ከገቡ ብዙ አስርት ዓመታትን ያስቆጠሩ ሲሆን አንዳቸው ሎላቸውን በውስጥ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት እንዲፈጠር እየሰሩ መሆኑን ይከሳሉ።

ኢትዮጵያ ከሶስት ዓመት በፊት በአፍሪካ ግዙፍ የሆነውን ታላቂ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በአምስት ቢሊዮን ዶላር በመገንባት ሀይል በማመንጨት ለራሷ ፍጆታ እና ለጎረቤት ሀገራት በመሸጥ ላይ ትገኛለች።

ግብጽ ይህ ግድብ የውሀ መብቴን ይጎዳል ብትልም ኢትዮጵያ ግን የአባይ ወንዝ 85 በመቶ ምንጭ መሆኗን ገልጻ በራሷ ሀብት የመጠቀም ሙሉ መብት እንዳላት አስታውቃለች።

ግብጽ ጉዳዩን እስከ ተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ድረስ በመውሰድ ክስ ያሰማች ቢሆንም ምክር ቤቱ ጉዳዩ በድርድር የሚፈታ መሆኑን ገልጿል።

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢትዮጵያ ግብጽ እና ሱዳንን በታላቁ ህዳሴ ግድብ ውሀ አጠቃቀም ዙሪያ ለማወያየት በይፋ ፍላጎታቸውን በተደጋጋሚ ቢገልጹም እስካሁን ድርድሩ አልተጀመረም።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *