በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ ከ100 በላይ ሰዎች በኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች መታገታቸውን የታጋቾች ቤተሰቦችና ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡
ታጣቂዎቹ ነዋሪዎችን ማገትና ማፈናቀል ከጀመሩ ረዥም ጊዜያት ቢቆጠሩም፣ በ2015 ግን ለተወሰኑ ወራት ፋታ አግኝቶ እንደነበር፣ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ እንደ አዲስ እንደተቀሰቀሰና በዚህም ነዋሪዎቹ እየታገቱ፣ እየተፈናቀሉና ቤት እየተቃጠለ ነው ሲል ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል፡፡
በኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ቁጥጥር ሥር የነበሩ የደራ ወረዳ ሰባት ቀበሌዎችን ከሁለት ወራት በፊት በተደረገ ዘመቻ ነፃ ማድረግ ተችሎ እንደነበር ያስረዱት ነዋሪዎቹ፣ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ግን ጥቃት ማገርሸቱን አክለው ገልጸዋል፡፡
ጋዜጣው በስልክ አነጋገርኳቸው ያላቸው አምስት የወረዳው ነዋሪዎች እንደገለጹት፣ የአካባቢው ነዋሪዎች በታጣቂ ቡድኑ እየተሰቃዩ መሆናቸውን፣ በርካታ ሰዎች በየቀኑ እየታገቱና እየተፈናቀሉ እንደሆኑ፣ የታገቱ ሰዎችን ለማስመለስም የሸኔ ታጣቂዎች እስከ 200 ሺሕ ብር እየጠየቁ ነው ተብሏል፡፡
ታጣቂ ቡድኑ ጥቃት እያደረሰ ያለው በወረዳው በሚገኙ ባቡ ደሬ፣ ማንቃታ፣ ጅሩ፣ አድዓ መልኬ፣ ከሩ ሲባ በተባሉ ቀበሌዎች እነደሆነ ተገልጧል፡፡
ተቀስቅሷል የተባለውን ጥቃት በተመለከተ የደራ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሺበሺ አያሌው፣ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ሰሞኑን ነዋሪዎችን በማገት ጥቃት እያደረሱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ሰኞ መጋቢት 18 ቀን 2015 ሦስት ሰዎች በታጣቂ ቡድኑ ታግተው የነበረ ቢሆንም፣ በተደረገ ክትትልና ዕርምጃ ጅማ በር ተብሎ ከሚጠራ ሥፍራ ሲደርሱ ማስመለስ እንደተቻለ የገለጹት አቶ ሺበሺ፣ ‹‹ንፁኃን ሰዎች በታጣቂዎች ሲታገቱ ወዲያው ከሰማን ለማስመለስ እንሠራለን፡፡ ካልሰማን ግን ምንም ማድረግ አይቻልም›› ብለዋል፡፡
ታጣቂዎቹ ሰዎችን አግተው አቦቴ የሚባል ጫካ ውስጥ እንደሚያስቀምጧቸው ያስረዱት የወረዳ አስተዳዳሪው፣ ታጣቂ ቡድኑ የሚያደርሰውን ጥቃት ለማስቆም የግድ ኃይል መጨመርና ዕርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግ፣ ይህን ለማድረግም የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ነዋሪዎቹ ባቡ ደሬ ቀበሌ የፌዴራል ፖሊስ ቢኖርም ታጣቂዎች የሚያደርሱት ጥቃት መከላከል አልቻለም ሲሉ የወቀሱ ሲሆን፣ አቶ ሺበሺ በበኩላቸው ከማክሰኞ መጋቢት 18፣ 2015 ጀምሮ ዕርምጃ እየተወሰደ ነው ብለዋል፡፡
የኦነግ ሸኔ ታጣቂ ቡድን በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋና የተለያዩ ዞኖች ጥቃት እንደሚያደርሱ የሚታወቅ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ትናንት መጋቢት 19፣ 2015 በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎችን በተመለከተ ከምክር ቤት አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ‹‹መንግሥት ከሸኔ ጋር ለመደራደር ባለፉት ጊዜያት ከአሥር ጊዜ በላይ ሙከራ አድርጓል፡፡ ከኦነግ ሸኔ ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት አለን›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡