በግብር ስወራ እና ሌሌች ወንጀሎች ምክንያት ታግደው የነበሩት የስፖርት ውርርድ ቤቶች ዳግም ስራ ሊጀምሩ እንደሆነ ተገልጿል።
ካፒታል ጋዜጣ እንደዘገበው ከሆነ የኢትዮጵያ ሎተሪ አገልግሎት ጥብቅ የቁጥጥር ማዕቀፍ እና ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የስፖርት ውርርድ እና ዲጂታል ሎተሪ አገልግሎቶችን በአዲስ መልክ ለማስጀመር አጠቃላይ ዝግጅቶችን እያደረገ ነው።
የኢትዮጵያ መንግሥት በስፖርት ውርርድ እና በዲጂታል ሎተሪ ኢንዱስትሪ ላይ ባደረገው የኦዲት ግኝት፣ ኦፕሬተሮች ለመንግሥት መክፈል የሚገባቸውን 27.5 ቢሊዮን ብር አለመክፈላቸውን ማረጋገጡን ተከትሎ፣ ዘርፉን በቴክኖሎጂ በተደገፈ የቁጥጥር ሥርዓት ውስጥ በማስገባት በድጋሚ ለማስጀመር ዝግጅት እያደረገ ይገኛል።
የኦዲት ረቂቅ መነሻ እንደሚለው፣ ፈቃድ ያላቸው የቤቲንግ ኦፕሬተሮች ከሐምሌ 2022 እስከ ታህሳስ 2025 ባለው ጊዜ ውስጥ ወደ 199 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ በሲስተማቸው ያንቀሳቀሱ ቢሆንም፣ ለመንግሥት መክፈል ከሚገባቸው ኮሚሽን ውስጥ እጅግ አነስተኛውን ብቻ ነው ገቢ ያደረጉት።
በዚህ ጊዜ ውስጥ ሊከፈል ከሚገባው 30 ቢሊዮን ብር ገደማ ኮሚሽን ውስጥ የተከፈለው 3.6 ቢሊዮን ብር ብቻ ነው። ይህም ማለት ኦፕሬተሮቹ ከሚጠበቅባቸው ክፍያ ውስጥ 12 በመቶውን ብቻ ሲከፍሉ፣ ከየአስር ብሩ ዘጠኝ ብሩን ለመንግሥት ገቢ አላደረጉም።
በምርመራው የተረጋገጠው አጠቃላይ የ27.5 ቢሊዮን ብር እዳ፣ ያልተከፈሉ ኮሚሽኖችን፣ ቅጣቶችን፣ የፈቃድ እድሳት እና የምዝገባ ክፍያዎችን ያካተተ ነው። ከዚህ እዳ ውስጥ “ዳሽ ቤቲንግ” የተባለው ድርጅት ብቻ 8.64 ቢሊዮን ብር (ከአጠቃላይ እዳው አንድ ሦስተኛውን) ያልተከፈለ ክፍያ እንዳለበት የኦዲት ውጤቱ ያሳያል። ሌሎች 10 ኩባንያዎች ደግሞ በጋራ ወደ 19 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ እዳ አለባቸው ተብሏል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሎተሪ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ቤዛ ግርማ ግኝቱን አረጋግጠው፣ የኦዲት ሂደቱ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ ከሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት ጋር በመተባበር ተገቢውን ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድ ገንዘቡን ለማስመለስ እንደሚሠራ ገልጸዋል።
የስፖርት ቤቲንግ ኢንዱስትሪው ከቁጥጥር ሥርዓቱ ምን ያህል ፈጥኖ እንዳደገ የሚያሳየው፣ እ.ኤ.አ. በ2022 ዓ.ም. በዓመት ውስጥ በዘርፉ ሲንቀሳቀስ የነበረው ገንዘብ 4.7 ቢሊዮን ብር ብቻ የነበረ ሲሆን፣ በመስከረም 2025 ግን ወርሃዊ የገንዘብ ዝውውሩ ወደ 20 ቢሊዮን ብር ከፍ ብሏል።
የዲጂታል ክፍያዎች እና የሞባይል ቴክኖሎጂ ተጠቃሚዎች በአካል ወደ ቤቲንግ ቤቶች ሳይሄዱ በስልካቸው ብቻ ገንዘብ እንዲያስገቡ፣ እንዲወራረዱ እና እንዲያወጡ አስችሏቸዋል።
ይሁን እንጂ የቁጥጥር ሥርዓቱ ከዚህ የቴክኖሎጂ ዕድገት ጋር እኩል ባለመጓዙ፣ በ2025 መገባደጃ ላይ መንግሥት በዘርፉ ላይ ጥብቅ እርምጃ እንዲወስድ አስገድዶታል።
የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ የተደበቀ ገቢን በተመለከተ ባደረገው ምርመራ በርካታ የቤቲንግ ፈቃዶችን የሰረዘ ሲሆን፣ የሕዝብና የግል አጋርነት የዲጂታል ሎተሪ ስምምነቶችንም አቋርጧል።
ፈቃድ ያላቸው ኦፕሬተሮች ቢዘጉም፣ የቤቲንግ ፍላጎቱ ባለመቆሙ ሕገ-ወጥ የውርርድ እንቅስቃሴዎች እና የውጭ ዌብሳይቶች በስፋት መቀጠላቸው ለመንግሥት ሌላ ፈተና ፈጥሯል።
ስለዚህ የአሁኑ የፖሊሲ አቅጣጫ “ቤቲንግ ሙሉ በሙሉ ይዘጋ?” የሚለው ሳይሆን፣ የመንግሥት ግብር የማይጭበረበርበት እና የደንበኞች ደህንነት የሚጠበቅበት ግልጽ ሥርዓት እንዴት ይፈጠር የሚለው ላይ ያተኮረ ነው። አቶ ቤዛ እንዳረጋገጡት፣ አገልግሎቱን “በአዲስ መልክ” ዳግም ለማስጀመር ዝግጅት እየተደረገ ነው።
የብሔራዊ ሎተሪ አገልግሎት አሁን ላይ ኦፕሬተሮችን ለመቆጣጠር የሚያስችል የተማከለ ዲጂታል ሲስተም እያለማ ነው።
ይህ ሲስተም ኦፕሬተሮች የሚያደርጉትን እውነተኛ የገንዘብ ዝውውር ከመንግሥት ኮሚሽን እና ክፍያዎች ጋር በቀጥታ በማስተያየት ቴክኖሎጂ-መር ቁጥጥርን ዕውን ያደርጋል።
በቀጣይ ወደ ገበያው መመለስ ለሚፈልጉ ኩባንያዎች ይህ አዲስ ሥርዓት ጠንካራ የክትትል መስፈርት ይዞ የሚመጣ ሲሆን፣ ባንኮች እና የዲጂታል ክፍያ አቅራቢዎችም ሕጋዊ እና ሕገ-ወጥ ኦፕሬተሮችን ለይተው ግብይቶችን እንዲያስተናግዱ ጥብቅ ኃላፊነት ይጣልባቸዋል ተብሏል።