ኢትዮጵያ በፕሬዚዳንት እንድትመራ በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ ተመካካሪዎች መግባባት መደረሳቸው ተሰምቷል።
ይሁንና ፕሬዚዳንቱ በሕዝብ ይመረጥ ወይስ በፓርላማ በሚለው ጉዳይ ተመካካሪዎች ስምምነት ላይ አለመድረሳቸው ተገልጿል።
ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ቀርቶ በፕሬዚዳንት እንድትመራ፣ የመንግሥት አደረጃጀትና ቅርጽ፣ እንዲሁም የፖለቲካ ሥርዓት፣ የፖለቲካ ውክልናና የምርጫ ሥርዓት አጀንዳ ላይ የ500 ቡድን ተመካካሪዎች ሙሉ በሙሉ በምክረ-ሐሳብ ደረጃ መግባባት ላይ ደርሰዋል ተብሏል።
በዚሁ አጀንዳ ላይ ተወያይ የነበሩ ተመካካሪዎች ለሪፖርተር በሰጡት አስተያየት፣ በቀረቡት አብዛኞቹ ምክረሐሳቦች መግባባት ላይ መደረሱን ሆኖም ያላግባቡና ወደ ቀጣይ የተሻገሩ ጉዳዮች መኖራቸውንም ገልጸዋል።
በዚህም የ500 ቡድን ተመካካሪዎች የአገሪቱ አስተዳደር ሥርዓት ፓርላሜንታሪ ሆኖ እንዲቀጥል፣ የአገሪቱ መሪ ፕሬዚዳንት እንዲሆን፣ አዲሱ ተመራጭ ፕሬዚዳንትም የጠቅላይ ሚኒስትሩና የፕሬዚዳንቱ ሥልጣንና ተግባርን ጠቅልሎ እንዲወጣ በምክረሐሳብ ደረጃ ከመግባባት ላይ መደረሱን፣ ይህም ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲቀር የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።
የአገሪቱ መሪ የሥልጣን ዘመን 6 ዓመት ሆኖ ለሁለት ዙር እንዲደረግ፣ የክልል መሪዎችም ከፌዴራሉ ጋር ተመሳሳይ እንዲሆን በምክረሐሳብ ደረጃ ከመግባባት ላይ መደረሱን ገልጸዋል።
የሕገመንግሥት ጉዳዮች ተርጓሚ ፍርድ ቤት እንዲቋቋም፣ አሁን ያለው የፌዴሬሽን ምክር ቤት አሠራር ያልመለሳቸው የማንነትና የራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄዎች “ሕብረ ብሔራዊ አንድነት ኮሚሽን” የሚል ሥያሜ ያለው ገለልተኛ ተቋም በአስቸኳይ ተቋቁሞ በአጭር ጊዜ ውስጥ ምላሽ እንዲሰጥባቸው ለዚህም ይረዳ ዘንድም ልዩ የባለሙያዎች ቡድን እንዲቋቋም በምክረሐሳብ ደረጃ ከመግባባት ላይ መደረሱ ተገልጿል።
ይህ በዚህ እንዳለም በፌደራል ከተማ ዋና መቀመጫ በሆነችው የአዲስ አበባ ከተማ ጉዳይ በቀረቡት ሁለት አማራጮች ላይ እስካሁን ከስምምነት ላይ እንዳልተደረሰ ተሰምቷል።