ኢትዮጵያ በተጠናቀቀው የ2018 በጀት ዓመት ውስጥ 1.5 ትሪሊዮን ብር ከግብር የሰበሰበች ሲሆን ከግል ድርጅቶች ሄኒከን ቢራ ቁጥር አንድ ግብር ከፋይ ተቋም ሆኗል።
ከአራት በላይ የቢራ ብራንዶችን ለኢትዮጵያ ገበያ በማምረት ላይ ያለው የጀርመኑ ሄኒከን ኩባንያ 26 ቢሊዮን ብር እንደከፈለ ተገልጿል። ሄኒከን እንደሀገር ከፍተኛ ግብር ከሚከፍሉ ተቋማት መካከል በአራተ ደረጃ ላይ ስሙ ተጠቅሷል።
በዚህ በጀት ዓመት ለመንግስት 10 ከፍተኛ ግብር ከፋይ ድርጅቶች መካከል 7ቱ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ናቸው።
ኢትዮ ቴሌኮም 66 ቢሊዮን ብር በመክፈል እንደ ሀገር ቁጥር አንድ ግብር ከፋይ ተቋም ነው።
ሁለተኛው ግብር ከፋይ ተቋም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲሆን ከፈለው 37 ቢሊዮን ብር ሲከፍል የኢትዮጵያ አየር መንገድ ደግሞ 31 ቢሊዮን ብር እንደከፈለ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ መርከብና ሎጅስቲክ ድርጅት ደግሞ 22 ቢሊዮን ብር ሲከፍል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል 18 ቢሊዮን ብር እንዲሁም አዋሽ ባንክ 15 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር መክፈሉ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት 13 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ሲከፍል ሌላኛው የቢራ አምራች ድርጅት ቢጂአይ ኢትዮጵያ 12 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ከፍሏል ተብሏል።
ይህ በዚህ እንዳለም በውርስ ወይም በስጦታ በሚገኙ ገቢዎች ላይ አዲስ የታክስ ዓይነት ሊጣል መሆኑ ተገልጿል።
ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሆኑ የውርስና የስጦታ ገቢዎች ለዚህ ታክስ እንደሚዳረጉ ተመልክቷል።
ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (IMF) የአምስተኛውን ዙር የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ሪፎርም ግምገማ ተከተሎ ይፋ ባደረገው ባለ 132 ገጽ ሙሉ ሪፖርት እንደጠቆመው፣ የአገሪቱ የታክስ መሠረት በጣም ጠባብ በመሆኑ መንግሥት በየዓመቱ የአገር ውስጥ ገቢውን ለማሳደግ አዳዲስ የታክስ ዓይነቶችን ለመተግበር አቅዷል።
በዚሁ ሪፖርት መሠረት በውርስና ስጦታ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ በሚገኝ ገቢ ላይ ታክስ ይጣላል።
በሲጋራ፣ በአልኮልና በነዳጅ ምርቶች ላይ የሚጣለው ታክስ እንደሚጨምር የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም አገራዊ ገቢን ከመጨመር ባለፈ ለጤና ፖሊሲዎች አተገባበር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ተመልክቷል።