በኢትዮጵያ ሙስና አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ ተገለጸ

የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ሙስናን አስመልክቶ ያለውን ግንዛቤ የተመለከተ የዳሰሳ ጥናት በማካሄድ፣ የመሬትና የገቢዎች ተቋማትን ጨምሮ በበርካታ ተቋማት ውስጥ ሙስና አሳሳቢ መሆኑን ማረጋገጡን አስታውቋል።

የመሬት አስተዳደርና የይዞታ ምዝገባ፣ የገቢዎችና ታክስ ጽሕፈት ቤቶች፣ የኮንስትራክሽን ፈቃድ ቁጥጥር፣ የንግድና ትራንስፖርት ቢሮዎች፣ የወረዳና የቀበሌ አስተዳደሮች በከፍተኛ ደረጃ ለሙስና ተጋላጭ መሆናቸው በጥናቱ ተለይቷል ብሏል፡፡

ኮሚሽኑ ለዳሰሳ ጥናት በተወሰደ ናሙና ከ60 በላይ የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን ሙስና በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ ተግባራት ከፍተኛ እንቅፋትና ችግር የፈጠረ አሳሳቢ ችግር መሆኑን እንደነገሩት ገልጿል፡፡

በአቋራጭ የመበልፀግ ፍላጎት፣ የሥነ ምግባር ጉድለት፣ ውስብስብና ግልጽ ያልሆኑ የአገልግሎት አሰጣጥ ሒደቶችና የሕግ ማስከበር ድክመቶች ለሙስና መስፋፋት ዋነኛውንና ቀዳሚውን ድርሻ እንደሚይዙ የኮሚሽኑ የጥናት ሪፖርት ያመለክታል፡፡

በጥናቱ ጉቦ ለመስጠት የሚገደዱ ሰዎች ለድርጊታቸው የሚያቀርቡት አንዱ ምክንያት አገልግሎቱን ለማግኘት ሌላ አማራጭ በማጣታቸው እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ግለሰቦች ጉቦ የሚሰጡት የሚፈልጉት አገልግሎት እንዲፈጸምላቸውና የሚጠበቅባቸውን ባለማድረጋቸው ሊደርስባቸው የሚችለውን እንግልት ለማስቀረት መሆኑን ጥናቱ ያመለክታል፡፡

የሙስና ድርጊትን ለመጠቆም የሚፈልጉ ግለሰቦች ሊደርስባቸው የሚችል የበቀል ዕርምጃና የማስፈራራት ሥጋት በመኖሩ፣ አስተማማኝ የጠቋሚዎች ጥበቃ ሥርዓት ማነስ፣ እንዲሁም የጥቆማ አሰጣጥ ሒደቱ ረዥምና ውስብስብ መሆን ኅብረተሰቡ ሙስና ለመጠቆም ሥጋት እንዳለበት በጥናቱ መገለጹ ተነግሯል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው እና በንግድ ሥርዓቱ ላይ እክል ፈጥረዋል በሚል በተጠረጠሩ አካላት ላይ ሰፊ እና የተቀናጀ የሕግ ማስከበር እርምጃ መወሰዱን ይፋ አድርጓል።

​የኮሙዩኒኬሽን ሚኒስትሯ ወይዘሮ እናትዓለም መለሰ በሰጡት መግለጫ፣ በንግድና ፋይናንስ ዘርፍ የታዩ ሕገ-ወጥ አሠራሮችን፣ የምርት እጥረቶችንና የዋጋ ንረትን ለመግታት በተካሄዱ የተቀናጁ ኦፕሬሽኖች ተከታታይ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ገልጸዋል።

​በተካሄዱት ኦፕሬሽኖች በሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር የተጠረጠሩ 169 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ውለዋል። በተጨማሪም ከ7,000 በላይ መጋዘኖችና የንግድ ድርጅቶች፣ 183 የኮንትሮባንድ ተሳታፊዎች እና 38 የቤቲንግ ድርጅቶች ላይ ሕጋዊ እርምጃና እገዳ ተጥሏል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *