ከደላሎች ውጪ ሰራተኞችን ከቀጣሪዎች ጋር በቀጥታ የሚያገናኝ መተግበሪያ ተዘጋጀ

የቤት ውስጥ ሰራተኛን ጨምሮ የግል አገልግሎት ሰራተኞች እና አሰሪዎችን የሚያገናኝ፣ ደላላን የሚተካ መተግበሪያ እየተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል።

የግል አገልግሎት ቅጥር የሚባሉትን እንደ አትክልተኛ፣ የቤት ውስጥ ተንከባካቢ፣ የቤት ውስጥ አብሳይ (ሼፍ) እና ሌሎችም ዘርፎች የቅጥር ግንኙነት ከደላላ ጣልቃ-ገብነት የሚያላቅቅ መተግበሪያ እና አዲስ ደንብ እየተዘጋጀ እንደሆነ ተገለጸ።

ዓለም አቀፍ የሥራ ድርጅት ኮንቬንሽን 189ን ታሳቢ አድርጎ የተዘጋጀው ደንብ ለፍትሕ ሚኒስቴር መቅረቡን እና በቅርቡ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ይጸድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር አስታውቋል።

አንድ ዓመት አካባቢ ለሚፈጅ ጊዜ ግብዓት በማሰባሰብ እና ባለድርሻ አካላትን በማወያየት የተዘጋጀው ደንብ፣ የቤት ሠራተኞች መመዝገቢያ ሶፍትዌር ሲስተም እንዲኖረው የሚያስችል መተግበሪያ እየተዘጋጀለት እንደሆነ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር የአሰሪና ሠራተኛ ጉዳይ ዘርፍ የኢንዱስትሪ ግንኙነትና የሥራ ሁኔታዎች ቁጥጥር መሪ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጥዑመ-እዝጊ በርሔ መናገራቸውን አሀዱ ራዲዮ ዘግቧል።

ስራ አስኪያጁ በማብራሪያቸው፤ አዲሱ አሰራር በተግባር ላይ በሚውልበት ጊዜ አሰሪ እና ሠራተኞች በመሀል ደላላ ሳያስፈልጋቸው በአፕሊኬሽን አማካኝነት ተገናኝተው በሕጋዊ ውል ቅጥር መፈጸም እንደሚችሉ ገልጸዋል።

በተጨማሪም፤ ከዚህ ቀደም በቤት ውስጥ ሰራተኛ እና አሰሪ መካከል ይፈጠር የነበረ አለመግባባት በፍትሐ ብሔር ይታይ እንደነበር አስታውሰው፤ አዲሱ ደንብ ለፍትሕ ሂደቱ አስቸጋሪ የነበረን አሰራር በማረም ጉዳዩ በአሰሪ እና ሰራተኛ አዋጁ እንዲታይ ያደርጋል ብለዋል።

ይህ መሆኑ የሠራተኛውንም ሆነ የአሰሪውን መብት እና ግዴታ ለማስጠበቅ እንደሚያግዝና ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮ በመውሰድ የተዘጋጀ መሆኑ ተመላክቷል። የደሞዝ ጉዳይን በተመለከተ ለጊዜው በአሰሪና ሠራተኛ ስምምነት የሚወሰን መሆኑ ተገልጿል። ለወደፊቱም ዝቅተኛ የደሞዝ ወለል ሲወሰን በዚሁ መሠረት የሚካተት ይሆናል ተብሏል።

የግል አገልግሎት ቅጥር የሚባሉት እንደ አትክልተኛ፣ የቤት ውስጥ ተንከባካቢ፣ የቤት ውስጥ አብሳይ ሼፍ እና ሌሎችም ዘርፎች በዚህ ሲስተም ውስጥ ይካተታሉ ተብሏል።
 

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *