ደረሰኝ የማይሰጡ ነጋዴዎች የ100 ሺህ ብር ቅጣት ይጠብቃቸዋል ተባለ

በግብይት ወቅት ማናቸውም ግብር ከፋይ ነጋዴ ያለደረሰኝ ሽያጭ ሲያከናውን ወይም ዋጋ አሳንሶ የተገኘ በእያንዳንዱ ደረሰኝ የአንድ መቶ ሺህ ብር ቅጣት መጣል የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ያለ ደረሰኝ ሲገበያይ የተገኘ ማንኛውም ግብር ከፋይ ለገዢ ባልሰጠው በእያንዳንዱ ደረሰኝ ብዛት ከዚህ ቀደም 50 ሺህ ብር ይቀጣ የነበረ ሲሆን አሁን ላይ ማሻሻያ በተደረገለት የታክስ አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ መሰረት ወደ አንድ መቶ ሺህ ብር ቅጣት ከፍ ብሏል።

የገንዘብ ሚኒስቴር እንደ ዋና ማሻሻያዎች ካነሳቸው መካከል የታክስ የምስክር ወረቀት አሰጣጥን ማሻሻል፣ የታክስ አለመግባባቶች ሲፈጠሩ በማስታረቅ ሥርዓት መፍታት፣ የታክስ ውሳኔ ማስታወቂያ የሚታረምበትን ሥርዓት ግልጽ ማድረግ፣ እንዲሁም የውሳኔ ማስታወቂያ ማሻሻያና የይግባኝ ማቅረቢያ የጊዜ ገደቦችን በግልጽ ማስቀመጥ የሚሉት ይገኙበታል።

እነዚህ ማሻሻያዎች በታክስ ከፋዩ እና በታክስ ባለሥልጣኑ መካከል ያለውን ግንኙነት ይበልጥ ቀልጣፋ ለማድረግ ያለመ ለውጥ በሚል ተመልክቷል።

የገንዘብ ሚኒስቴር ዛሬ ግንቦት 10 ፣ 2018 ዓ.ም በረቂቅ አዋጁ ላይ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተወያይቷል።

በውይይቱ ላይ የተገኙ ተሳታፊዎች ቅጣቱ በእጥፍ ማደጉን ተቃውመዋል።

በተጨማሪም በአንድ ግብይት በሚሰጥ ተመሳሳይ ደረሰኝ ላይ የተለያዩ ዋጋዎችን በመመዝገብ የሽያጭ ዋጋን ያሳነሰ እና ዋጋውን አሳንሶ ደረሰኝ የቆረጠ ማንኛውም ሰው አንድ መቶ ሺህ ብር የገንዘብ መቀጫ የሚያሰቀጣ ይሆናል።

ይህንኑ ተግባር የፈፀመ ከአምስት እስከ ሰባት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ይጠብቀዋል ሲል ረቂቅ የማሻሻያ አዋጁ ደንግጓል።

ይህ ተግባራዊ ሊሆን የሚችለው ደረሰኝ ባለመስጠት ወንጀል ተጠያቂ የሚሆነው የወንጀሉ ድርጊት የተፈጸመው በአንድ የግብር ዘመን ውስጥ ለሁለት ጊዜያት ያህል አስተዳደራዊ ቅጣት ከተቀጣ በኋላ በሚሆንበት ጊዜ ነው ሲል አሰቀምጧል።

የረቂቅ አዋጁን ዓላማ እና ምንነት ለተሳታፊዎች ያስረዱት የሚኒስትሩ ከፍተኛ አማካሪ ዋሲሁን አባተ ደረሰኝ አለመስጠት አሁን ላይ የንግዱ ማህበረሰብ እየተላመደው የመጣ ለማንኛውም አካላት የማይጠቅም ድርጊት ነው ብለዋል።

ደረሰኝ አለመስጠት ለመንግስት ብቻ ሳይሆን ነጋዴውንም እዳ ውስጥ ከቶታል ያሉት አማካሪው ደረሰኝ አለመስጠት ከባድ መዘዝ ይዞ የሚመጣ መሆኑን አስጠንቅቀዋል።

አማካሪው አክለውም አንዳንድ ግብር ከፋይ ድርጅቶች ደረሰኝ ሳይሰጡ ቀርተው ሲጠየቁ ሰራተኞቻቸው ላይ ሊጥሉ ይሞክራሉ በማለት ማናቸውም ድርጅት የሚቀጥረውን ሰራተኛ ያለ ደረሰኝ ሽያጭ ማከናወን እንደማይቻል ማሰወቅ አለበት ብሏል።

ከዚህ ቀደም የነበረው ቅጣት እንዲቀል ተደርጓል ያሉት አማካሪው አንድ የድርጅት ኃላፊ ማሰር ቢዝነሱን እና ቤተሰቡን ማሰር ይሆናል በማለት፣ ይህ ደግሞ ኢኮኖሚውን ይጎዳል ያሉ ሲሆን ቅጣቱ አስፈላጊ ስለሆነ ያለ ደረሰኝ ግብይት ሲፈፅም የተገኘ ህጉን ተግባራዊ ማድረግን ግደታ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ማናጀሩ በደረሰኝ ያልተሸጠ ገንዘብ ማታ ኪሱ ውስጥ እያሰገባ እኔ አላውቅም ነበር ማለት አይችልም ሲሉ አማካሪው ለተሳታፊዎቹ ተናግረዋል።

አማካሪው አክለውም ቅጣት በዛ ለሚለው ጥያቄ መልስ የሰጡ ሲሆን አሁን ያለው መቅጣትና አስተማሪም መቀጣጫ አልሆነም ያሉ ሲሆን አሁን ላይ የተሻሻለው ቆንጠጥ አድርጎ እንዲይዝ የታሰበ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በዓለም ባንክ ምክረ ሀሳብ ገቢ የሚያስገኙ አማራጮችን በየጊዜው እያሰፋች የመጣች ሲሆን ባሳለፍነው በጀት ዓመት በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአንድ ትሪሊዮን በላይ ብር ከግብር መሰብሰብ ችላለች።

ዓለም ባንክ እና ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ድርጅት አይኤምኤፍ አኩንም ኢትዮጵያ ተጨማሪ የገቢ ማግኛ ማሻሻያዎችን እንድታደርግ በመወትወት ላይ ናቸው።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *