የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በካናዳ ከሚገኘው ፊውቸር ፊት ኢንተርናሽናል (FFI) ጋር በክህሎት ልማትና ሥራ ዕድል ፈጠራ መስኩ በጋራ መስራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል።
ስምምነቱ ለኢትዮጵያውያን ወጣቶች የክህሎት ልማትን ለማጠናከር፣ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እና ዓለም አቀፍ የሥራ ዕድሎችን ለማመቻቸት ዕድል የሚፈጥር መሆኑ ተገልጿል።
በመርሃ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል፣ ከኢንቨስትመንቶች ሁሉ ትልቁ ኢንቨስትመንት የሰው ኃይል ልማት ላይ የሚደረግ ኢንቨስትመንት ነው፡፡
ስምምነቱ የሥራ ዕድል ከማመቻቸት ባሻገር ወጣቶችን በስልጠና ማብቃት ላይ ያተኮረ በመሆነ በኢትዮጵያ ወጣቶች ላይ የሚደረግ የረጅም ጊዜ ኢንቨስትመንት ነው ብለዋል።
ይህም የዜጎችን እምቅ አቅም በመፍጠር ለዓለም አቀፍ የሥራ ገበያ ከማቅረብ ባለፈ አጠቃላይ የሰሪ ኃይላችንን የሚያጠናክር እንደሆነም ሚንስትሯ አብራርተዋል።
የስራ ምዝገባም ሆነ ስምሪት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ የሚደረገው በኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ስርዓት (lmis.gov.et) አማካኝነት ብቻ ነው ብለዋል፡፡
የፊውቸር ፊት ኢንተርናሽናል ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ አብይ ራይሞንድ በበኩላቸው፣ ስምምነቱ በወጣቶቻችን ክህሎት እና በዓለም አቀፉ የሥራ ገበያ ፍላጎት መካከል ድልድይ የሚሆን ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከፍተኛ አቅም እንዳላት አመላክተው ይህ አቅም ግን በተገቢው መልኩ ጥቅም ላይ እንዳልዋለ አመላክተዋል፡፡
ይህ አጋርነት በኢትዮጵያ የሥራ ዕድል ፈጠራን እና የኢኮኖሚ እድገትን የሚያሰፋ፣ በሌላ በኩል በካናዳ ያለውን የሠራተኛ እጥረት ለመቅረፍ የሚረዳና የሁለቱንም ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነት ያረጋግጣል እንደሆነም ጠቁመዋል።
በእድሉ ተጠቃሚ መሆን ለሚፈልጉ ዜጎች በድርጅቱና በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ማህበራዊ ትስስር ገፆች እና በዋና ዋና የብዙሃን መገናኛ ተቋማት አማካኝነት እንደሚወጣ ገልፀው ከዚህ ውጪ በየትኛውም ግለሰብም ሆነ ድርጅት ማህበራዊ ትስስር ገጽ አማካኝነት ማስታወቂያው እንደማይወጣ እና ምዝገባ እንደማይካሄድ ገልፀዋል፡፡
በኢትዮጵያ የካናዳ አምባሳደር ክቡር ኒኮላስ ሪቻርድሰን በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያና ካናዳ የ60 ዓመታት የዲፕሎማሲ ግንኙነታቸውን እያከበሩ ባሉበት ወቅት የተፈረመው ይህ ስምምነት በሁለቱ ሀገራት መካከል እያደገ የመጣው የኢኮኖሚ ትብብር አካል መሆኑን ገልጸውታል።
ከቪዛ ጋር በተያያዘ የሚያጭበርብሩ አካላት መኖራቸውን አስታውሰው ህብረተሰቡ ላላስፈላጊ ወጪና እንግልት እንዳይዳረግ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል።
ቪዛ የሚሰጠው በካናዳ የኢሚግሬሽን፣ ስደተኞች እና ዜግነት አገልግሎት (IRCC) ብቻ ነው ያሉት አምባሳደሩ ግለሰብም ሆነ ማንኛውም ድርጅት ቪዛ መስጠት አይችልም። ጉዳዩን ቀላል እናደርጋለን የሚሉ አካላትን የሚያጭበረብሩ በመሆናቸው ሁሉም ጥንቃቄ ማድረግ አለበት ሲሉም አብራርተዋል፡፡