ኢትዮጵያ የማርበርግ ወረርሽኝን መቆጣጠሯን አስታወቀች

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ተከስቶ የነበረው የማርበርግ ቫይረስ (Marburg Viral Disease) ወረርሽኝ ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር መቻሉን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

ሚኒስቴሩ ከኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመሆን ፣ ወረርሽኙ ለመጀመሪያ ጊዜ መከሰቱ በይፋ ከተነገረበት ከሕዳር 5 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ሰፊ ስራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል።

በወረርሽኙ ወቅት በአጠቃላይ ለ3 ሺህ 800 ሰዎች የላብራቶሪ ምርመራ የተደረገ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ ቫይረሱ የተገኘባቸው 14 ሰዎች ነበሩ።

ከታካሚዎቹ መካከል ዘጠኙ በበሽታው ምክንያት ሕይወታቸው ሲያልፍ፣ አምስቱ ደግሞ ተገቢውን ሕክምና አግኝተው ማገገም መቻላቸው ይታወቃል።

ወረርሽኙን በአጭር ጊዜ ለመቆጣጠር እንዲቻል የክትትልና ምላሽ ስርዓት ተዘርግቶ ሲሰራ መቆየቱን የገለጸው ሚኒስቴሩ በተለይም ከ4 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ተጓዦች በመውጫና መግቢያ ኬላዎች ላይ የልየታ ምርመራ ሲደርግ መቆየቱ ተገልጿል፡፡

እንዲሁም ከ20 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ ከፖሊዮ ዘመቻ ጋር ተቀናጅቶ መከናወኑን የጤና ሚኒስትር ገልጿል።

በተጨማሪም ከታማሚዎች ጋር ንክኪ የነበራቸው 886 ሰዎች የቅርብ ክትትልና የመከላከያ ሕክምና ተደርጎላቸው ወደ ማህበረሰቡ መቀላቀላቸውን ጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር በሀገሪቱ ተከስቶ የነበረውን አስጊውን የማርበርግ ቫይረስ በሽታ (MVD) ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር መቻሉን ዛሬ ባዘጋጀው የማብሰሪያ መርሐ ግብር ላይ በይፋ አስታውቋል።

ወረርሽኙን ለመቆጣጠር በተደረገው ጥረት ዋነኛ ተሳታፊ ለነበሩ የጤና ባለሙያዎች እና አመራሮች የእውቅና እና ምስጋና ፕሮግራም ተካሂዷል፡፡

ለወረርሽኙ የተሰጠው ፈጣን ምላሽ ሥርዓት፦ ቫይረሱ በተገኘባቸው አካባቢዎች የተዘረጋው ጥብቅ የክትትል (Contact Tracing) እና የለይቶ ማቆያ ሥራ ወረርሽኙን በአጭር ጊዜ ለመግታት አስችሏል ተብሏል።

የአጋርነት ሚናን ከመፍጠር አንጻር ደግሞ ከዓለም ጤና ድርጅት (WHO) እና ከአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል (Africa CDC) ጋር የተደረገው የተቀናጀ የላቦራቶሪና የሎጂስቲክስ ድጋፍ ለውጤቱ ትልቅ አቅም እንደሆነም ተገልጿል።

ይሁንና አሁንም ወረርሽኙን መቆጣጠር መቻሉ ጥሩ ቢሆንም የጤና ባለሙያዎችና ዓለም አቀፍ ጥናቶች የቫይረሱ ባህሪ በተለይም ፈዋሽ መድሃኒት አለመገኘቱ፣ እንደ ሌሊት ወፍ አይነት የዱር እንስሳት ውስጥ ለረጅም ጊዜ ተደብቆ መቆየት መቻሉ ቫይረሱ ዳግም የመከሰት እድል ሊኖረው ስለሚችል ጥንቃቄ መደረግ እንደሚገባ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ተናግረዋል፡፡

የማርበርግ ቫይረስ እስከ 88 በመቶ የመግደል አቅም ያለው ሲሆን ከዚህ በፊት በማርበርግ ቫይረስ ተጠቅተው የቫይረሱን ስርጭት ተቆጣጥረናል ባሉ እንደ ታንዛንያ፣ ሩዋንዳ እና ኢኳቶሪያል ጊኒ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ዳግም በማርበርግ ቫይረስ ተጠቅተዋል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *