የባንኮች ብድር ዕድገት ጣሪያ ወደ 24 በመቶ አደገ

ብሔራዊ ባንክ አሁን ያለውን የዋጋ ግሽበት የመርገብ አዝማሚያ ለማስቀጠል እና የፋይናንስ ዘርፉን ጤናማነት ለመጠበቅ በመስከረም ወር ላይ ሊነሣ ይችላል ተብሎ የተገመተዉ የባንኮች ዓመታዊ የብድር ዕድገት ጣሪያን ሙሉ ለሙሉ ከማንሳት ይልቅ ገደቡ ለጊዜው ከ18 በመቶ ወደ 24 በመቶ ከፍ እንዲል ወስኗል፡፡

የባንኮች የብድር ዕድገት ገደብ መነሣት የብሔራዊ ባንክን የገንዘብ ፖሊሲ አቋም ለማመልከትና የገንዘብ ፖሊሲ መዋቅሩን የተሻለ ለማድረግ እንደሚረዳ ይታመናል ሲል ኮሚቴው አስረድቷል፡፡

ኮሚቴው  በጉዳዩ ላይ በወደፊት ስብሰባዎቹ ገምግሞ የውሳኔ ሐሳብ አንደሚያቀርብም ጠቅሷል፡፡

የብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ ተመን አሁን ባለበት 15 በመቶ እንዲቆይም ወስኗል፡፡

ብሔራዊ ባንክ ለሚሰጣቸው የተቀማጭ ሂሳብ አገልግሎት እና የብድር አገልግሎት የሚከፈሉ የወለድ ተመኖች ባሉበት እንዲቀጥሉ፤ እንዲሁም ባንኮች በብሔራዊ ባንክ የሚያስቀምጡት የግዴታ መጠባበቂያ ምጣኔ በነበረበት እንዲቆይ መወሰኑ ተጠቅሷል፡፡

ብሔራዊ ባንክ የዋጋ ግሽበቱ በሚፈለገው ልክ እንዲሆን ለማስቻል እንደ አስፈላጊነቱ ገበያ-መር የሆነ የገንዘብ ፖሊሲ መሣሪያዎችን በተናጠልም ሆነ በቅንጅት ወደፊትም እንደሚጠቀም የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ አስረድቷል፡፡

ዓመታዊ የዋጋ ግሽበት በተከታታይ እየቀነሰ በመምጣት ነሐሴ ወር 2017 ዓ.ም መጨረሻ 13.6 በመቶ ደርሷል ተብሏል፡፡

ለዋጋ ግሽበት መቀነስ ብሔራዊ ባንክ ተግባራዊ እያደረገ ያለው ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ፣ የግብርና ምርታማነት መሻሻል እና መንግሥት ዋጋን ለማረጋጋት እየወሰዳቸው ያሉ አስተዳደራዊ እርምጃዎች  ዐበይት ምክንያቶች ሆነው በኮሚቴው ተጠቅሰዋል፡፡

ምግብ-ነክ የዋጋ ግሽበት ነሐሴ ወር 2017 ዓ.ም መጨረሻ 12.7 በመቶ የደረሰ ሲሆን፣ ይህም ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ከነበረው የ18.8 በመቶ ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ቅናሽ አሳይቷል ተብሏል፡፡

በአንጻሩ፣ ምግብ-ነክ ያልሆነ የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር መጠነኛ ጭማሪ በማሳየት 15.1 በመቶ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ለዚህም በቅርቡ የተካሄደው የውጭ ምንዛሪ ተመን ለውጥ ጫና በተወሰነ መልኩ አስተዋጽኦ አድርጓል የተባለ ሲሆን በተመሳሳይ መልኩ፣ ነሐሴ ወር 2017 ዓ.ም መጨረሻ ወርሃዊ የዋጋ ግሽበት ወደ 1.1 በመቶ ዝቅ ማለቱ የዋጋ ግሽበቱ በኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ እየቀለለ መሄዱን ያመላክታል ሲል ብሔራዊ ባንክ በመግለጫው ላይ ጠቅሷል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *