ኢትዮጵያ የ6 መርከቦች ግዥ መፈፅሟ ተገለ

የመርከቦቹ መገዛት በባህር ትራንስፖርት ላይ ያላትን አቅም የበለጠ ያሳድጋል ተብሎ ታምኖበታል፡፡

የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ የሚያስተዳድራቸው 10 መርከቦች ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ የማዳበሪያ ምርትን ጨምሮ የሚበዛውን ምርት የምታጓጉዘው እነዚህኑ መርከቦች ተጠቅማ ነው።

አሁን ደግሞ የተጨማሪ ስድስት ትላልቅ መርከቦች ግዢ ተፈፅሞ ኢትዮጵያ መርከቦቹን ዘንድሮ እንደምትረከብ ተነግሯል።

ይህም ኢትዮጵያ በውሃ ትራንስፖርት ላይ ያላትን አቅም የሚያሳድግ ነው ተብሏል።

ከስድስቱ መርከቦች ሁለቱ እስከ 62,000 ቶን የመጫን አቅም ያላቸው እንደሆኑም ተነግሯል።

ኢትዮጵያ አሁን ካሏት አስር መርከቦች አባይ ሁለት በመባል የምትጠራው እስከ 63,000 ቶን የመጫን አቅም እንዳላት ይነገራል።

ባለፈው ዓመት ኢትዮጵያ ወደ ሀገር ውስጥ ካስገባችው 1.9 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን የማዳበሪያ ምርት አብዛኛው ተጓጉዞ ጅቡቲ ወደብ የደረሰው በራሷ መርከቦች ተጓጉዞ ነው ተብሏል።

ከሶስት ወራት በፊት የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ (ኢባትሎ) የአስር መርከቦች ባለቤት የመሆን ግቡን ለማሳካት በሚደረገው ጥረት፣ አዳዲስ መርከቦችን ለመግዛት ማቀዱን እና ለዚህም ከሀገር ውስጥ ባንኮች የገንዘብ ድጋፍ ማግኘቱን መግለጹ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ አዋሽ ባንክ እና ዳሽን ባንክ ይህንን ግዙፍ ግዢ በጋራ ለመደጎም መስማማታቸው ተገልጿል።

ኢባትሎ አዲስ ሁለት የአልትራማክስ ሁለገብ የደረቅ ጭነት መርከቦችን ለመግዛት በወቅቱ ጨረታ ያወጣ ሲሆን፣ በተጨማሪም አራት ያገለገሉ መካከለኛ መጠን ያላቸው መርከቦችን በመርከብ ደላሎች በኩል ለመግዛት ማቀዱንም ገልጾ ነበር።

የፋይናንስ ስምምነቱ ዝርዝር እንደሚያሳየው፣ አዋሽ ባንክ እና ዳሽን ባንክ ለአንድ ሁለገብ መርከብ እና ለአንድ የአልትራማክስ ደረቅ ጭነት መርከብ የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋሉ።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሌላ በኩል አዲስ የአልትራማክስ ሁለገብ እና ሁለቱን ያገለገሉ ኮንቴይነር መርከቦችን ጨምሮ የሦስት ተጨማሪ መርከቦችን ግዥ ለመደገፍ ተስማምቷል።

በአጠቃላይ፣ ኢባትሎ ለአምስቱ መርከቦች ጠቅላላ ወጪ 30% የሚሆነውን በራሱ የሚሸፍን ሲሆን፣ ቀሪው 70% በባንኮቹ ይሸፈናል። ከዚህም ባሻገር፣ አንድ መርከብ በሙሉ በተቋሙ ፋይናንስ እንደሚደረግ ተገልጿል።

ኢባትሎ ያገለገሉትን አራት መርከቦችን በቅርብ ጊዜ ውስጥ ለመረከብ ሲጠብቅ፣ የአዲሶቹ ሁለት ሁለገብ መርከቦች ግንባታ ግን የጨረታ ሂደቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ቢያንስ ሁለት ዓመታትን ይወስዳል ተብሎ ይገመታል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *