በህዳሴው ግድብ ግንባታ ወቅት 15 ሺህ ኢትዮጵያዊያን መሞታቸው ተገለጸ

የውሀ እና ኢነርጂ ሚንስትር ሀብታሙ ኢተፋ ከሪፖርተር መጽሄት ጋር በነበራቸው ቃለ መጠይቅ ላይ እንዳሉት በታላቂ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ወቅት 15 ሺህ ዜጎች ህይወታቸውን አጥተዋል።

ህይወታቸውን ካጡ ዜጎች መካከል የቀድሞው የግድቡ ግንባታ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ስመኘው በቀለ አንዱ ሲሆኑ ለብቻቸው መታሰቢያ ሀውልት እንደማይቆምላቸውም ሚንስትሩ ተናግረዋል።

“የጸጥታ ሀይሎች፣ ሹፌሮች፣ ሰራተኞች እና ሌሎሽም የህብረተሰብ ክፍሎች ህይወታቸውን አጥተዋል ስለዚህ ይህ በሆነበት ሁኔታ ለግለሰቦች የተለየ መታሰቢያ ሀውልት የለም” ሲሉም ሚንስትሩ በቃለ መጠይቁ ወቅት ገልጸዋል።

በግዝፈቱ ከአፍሪካ ቁጥር አንድ የሆነው የህዳሴው ግድብ በሚቀጥለው ሳምንት እንደሚመረቅ ይጠበቃል።

ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ከሰሞኑ በኢትቪ በተላለፈ ንግግራቸው ለግድቡ ግንባታ አስተዋጽኦ ያደረጉ አካላትን አመስግነዋል።

የቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ እና ሀይለማርያም ደሳለኝ ደግሞ ምስጋና ከቀረበላቸው የቀድሞ መሪዎች መካከል ዋነኞቹ ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ (ዶ/ር) በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ዙሪያ አስመልክቶ ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ላይ እንዳሉት የህዳሴው ግድብ ውሃ ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያ አፈር ወደ ሱዳን እና ግብጽ እየሄደ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቃለ መጠይቁ ላይ እንዳሉት “እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የማውቀው አባይ ውሃ፣ አፈር ፣አሳ እና ግንዳችንን ይዞ እንደሚሄድ ነበር፣ ነገር ግን አባይ ወርቃችንንም ጭምር እንደሚወስድ በቅርቡ በያዝነው ውሃ ውስጥ ባለው አፈር ላይ ባደረግነው ፍተሻ አረጋግጠናል” ብለዋል፡፡

“ለዘመናት ለታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ለሰጠነው ተመስግነን አናውቅም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጣራ እና ኩልል ያለ ውሃ እንደተለመደው መፍሰሱን እንዳላቆም ተናግረዋል፡፡

አባይ ወንዝ ላይ ግንባታ በመጀመራችን ይደረግ የነበረው ጫና ኢትዮጵያ ሀይል ብታመርት ምን ችግር ነበረው ብለን እንድንጠይቅ የሚያደርግ እንደነበርም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል።

“ለቁማር ቤቶች ሳይቀር ብድር በሚለቀቅበት ዓለም ውስጥ እየኖርን እኛ ግን ሀይል ለማመንጨት ስንጠይቅ ስንከለከል ኖረናል” ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም ግድቡን እውን በማድረጋችን የዘመናት ቁጭታችንን ማበስ ብቻ ሳይሆን ብርሃን እና ብስራትን መገኘቱን በቃለ መጠይቁ ላይ ተናግረዋል፡፡

የግድቡ ግንባታ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት፣ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፣ በዓለም የነዳጅ እና ብረት ዋጋ መጨመር፣ በቀይ ባህር ቀውስ እና ሌሎችም ስጋቶች ተደቅነውበት የነበረ ቢሆንም በተደረገ የዕለት ተዕለት ክትትል መሳካቱም ተገልጿል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የግድቡ ግንባታ መጠናቀቅ እውን እንዲሆን ላደረጉ ሰራተኞች፣ የጸጥታ ሀይሎች፣ ለሚዲያ ባለሙያዎች፣በግንባታው ላይ የተሳተፉ እንደ ሳሊኒ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ያሉ ተቋማትን ጨምሮ ለቀድሞ የሀገር መሪዎችም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *