የኢምግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በ2017 በጀት ዓመት ለ1.4 ሚሊዮን ዜጎች ፓስፖርት መስጠቱን አስታውቋል።
የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት እንዳሉት ለፓስፖርት አመልካቾች የተቀላጠፈ አገልግሎት በመሰጠቱ ምክንያት የአመልካቾች ቁጥር ቀንሷል ብለዋል።
ተቋሙ የኢ-ፓስፖርት ለመስጠት ያስቀመጠውን እቅድ በአዲስ አበባ ጎተራ ባለው ቅርንጫፍ ማስጀመሩም ተገልጿል።
ይሁንና ተቋሙ ፓስፖርት ቤት ለቤት መስጠት እጀምራለሁ በሚል የያዘው እቅድ እስካሁን ስለመጀመሩ ዳይሬክተሯ አልገለጹም።
ይህ በዚህ እንዳለም የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ከ3800 በላይ ሰዎች በተጭበረበረ ሰነድ ፓስፖርት ለማውጣት ሲሞክሩ በቁጥጥር ስር ውለዋል ተብሏል።
ተቋሙ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ፓስፖርት ለማግኘት የሚሞክሩ ሰዎችን የመቆጣጠሩ አቅሙ ያደገው ተቋማዊ ደህንነትን የማረጋጫ ሥርዓት ዘርግቷልም ተብሏል።
ከፓስፖርት አገልግሎት ጋር በተያያዘ ከሰራተኞች ጋር በመመሳጠር ተገልጋዮችን በማጉላላት እና ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ሞክረዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር እየዋሉ እንደሆነም ተገልጿል።
ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ዜጎች ከተፈቀደላቸው ጊዜ በላይ ከቆዩ ቅጣት እንደሚጠብቃቸው ከሰሞኑ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ማሳሰቡ ይታወሳል።