ዳሸን ባንክ ከእንግሊዝ እና ኔዘርላንድ ባንኮች 40 ሚሊዮን ዶላር ብድር አገኘ
የእንግሊዝ ዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንት (ቢ አይ አይ) እና የኔዘርላንድ የሥራ ፈጠራና ልማት ባንክ የሆነው (ኤፍ ኤም ኦ) እያንዳንዳቸው 20 ሚሊየን ዶላር በድምሩ 40 ሚሊየን ዶላር ብድር ለዳሸን ባንክ ማቅረባቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡
የብድር አቅርቦቱ ኢትዮጵያ ለውጪ ገበያ የምታቀርበውን የግብርና ምርት ለማሳደግ እና በእጅጉ አስፈላጊ የሆነውን የውጪ ምንዛሬ አቅርቦት ለማሻሻል እንደሚያስችል ተመላክቷል፡፡
ቢ አይ አይ እና ኤፍኤምኦ ለዳሸን ባንክ ያቀረቡት ገንዘብ በኢትዮጵያ 80 በመቶ የህብረተሰብ ክፍል በተሰማራበት፣ ለጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት 39 በመቶ ድርሻ ላለው እና ለወጪ ንግዱ 90 በመቶ አስተዋጽኦ ለሚያበረክተው የግብርና ዘርፍ ከፍተኛ እገዛ እንደሚኖረውም ታምኖበታል፡፡
የቀረበው ብድር ባንኩ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማሳደግ ለሚያደርገው ጥረት የበኩሉን እገዛ ያደርጋል ተብሏል።
ብድሩ በተለይም በእርሻ ሥራ ላይ ለተሰማሩ ምርታማነትን ለመጨመር የሚያስችሉ ግብአቶችን በማሟላት ከውጪ ገበያ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ተገልጿል፡፡
በዚህ ትብብር ቢአይአይ እና ኤፍኤምኦ ከዳሸን ባንክ ጋር በአመራር ስጋት አስተዳደር፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በማህበራዊ እና ስርዓተ- ጾታ ዘርፎች ዙሪያ ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን በኢትዮጵያ ለማስተዋወቅ እና ለማስረፅ በቅርበት እንደሚሰሩም ተመላክቷል፡፡