በምስራቅ ጎጃም ዞን ዋና ከተማ ደብረማረቆስ ከአርብ ነሐሴ 19/2015 እስከ ሰኞ ነሐሴ 22/2015 ድረስ በመከላከያ ሠራዊትና እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በተደረገ ውጊያ፤ ከመቶ በላይ ሰዎች ሳይገደሉ እንዳልቀረ ተገልጿል።
ሥማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ የደብረማርቆስ ስፔሻላይዝድ ሆሰፒታል ሐኪም በከተማዋ ቦሌ ተብሎ በሚጠራው ሰፈር ከመቶ በላይ ሰዎች መገደላቸውን ተናግረዋል ።
የሟቾቹ አስክሬን ከኹለት ቀን በላይ ሳይነሳ መንገድ ላይ ወድቆ መታየቱንም ነዋሪዎች እና ሀኪሞች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
“በቦታው የወደቁትን አስከሬኖች፤ አንዳንድ ሰዎች ሙስሊሙንም ክርስቲያኑንም ኹሉንም እያነሱ ማሪያም ቤተክርስቲያን ውስጥ እና በአካባቢ ቀብረዋቸዋል፡፡ ነገር ግን ሰኞ ድረስ ያልተቀበሩም ነበሩ።” ሲሉ ነዋሪዎቹ ጠቅሰዋል፡፡
በከተማው ለሦስት ቀናት በተደረገው ውጊያ ቆስለው ወደ ሆስፒታል የሄዱ ጥቂት ሰዎች ቢኖሩም፤ የትራንሰፖርት እና የሰው እንቅስቃሴ ባለመኖሩ የቆሰሉ ሰዎችን ወደ ሆስፒታል የሚወስዳቸው ጠፍቶ ሕይወታቸው ያለፉ ብዙዎች መሆናቸውንም ሐኪሟ ገልጸዋል።
የደብረማርቆስ አጠቃላይ ስፔሻላይዘድ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ አንዷለም ገረመው፤ ከአርብ ነሐሴ 19 እስከ ሰኞ ነሐሴ 22/2015 ድረስ 25 ሰዎች ቆስለው ወደ ሆስፒታል መግባታቸውን በመጥቀስ፤ “ከእነዚህ ውስጥ ሦስቱ ወዲያውኑ ሕይወታቸው አልፏል።” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ሥራ አስኪያጁ አክለውም፤ “በተኩስ ልውውጡ ቆስለው ወደ ሆስፒታል የገቡትና ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎች እድሜያቸው ከ17 እስከ 50 ዓመት የሆናቸውና ሰዎች ናቸው።” ካሉ በኋላ፤ በሆስፒታሉ ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን ጠቁመዋል።
በተጨማሪም በአካባቢው እየተካሄደ ባለው ወጊያ “ባለሙያዎቻችን ሥራቸውን እንደፈለጉ ተንቀሳቅሰው መስራት አልቻሉም፤ ታካሚዎችም ወደ ሆስፒታል ገብተው እየታከሙ አይደለም” ብለዋል።
ይህን ተከትሎም በተለይ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ታካሚ የሆኑ ሰዎች ወደ ተቋሙ መጥተው እየታከሙ አይደለም ያሉት ሥራ አስኪያጁ፤ “የመድኃኒት እጥረት እያጋጠመን በመሆኑ፣ የጸጥታ ችግሩ በዚህ የሚቀጥል ከሆነ ሆስፒታሉ ትልቅ ችግር ውስጥ ይገባል።” ሲሉ አክለዋል።
ከደብረማርቆስ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በተጨማሪ አጎራባች የሆኑ ስምንት የመጀመሪያ ደረጃ ሆሰፒታሎች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ የሪፈር ሕክምና የሚያስፈልጋቸው ታካሚዎች የትራንስፖርት አገልግሎት ባለመኖሩና ወደ እኛ ሆስፒታል መምጣት ባለመቻላቸው ችግር ላይ መውደቃቸውን ተናግረዋል ።
በደብረማርቆስ ባለፉት አራት ቀናት በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በተፈጠረው ግጭት በከተማዋ የሰው እና የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ አለመኖሩም ተጠቁሟል።
በአማራ ክልል በርካታ አካባቢዎች በሀገር መከላከያ እና ፋኖ መካከል አሁንም ከባድ ውጊያ እየተካሄደ እንደሆነ ከነዋሪዎች ሰምተናል።
ከትናንት በስቲያ በደቡብ ጎንደር ዞን ደብረታቦር ከተማ በከተማ ውስጥ በተካሄደ ውጊያ ንጽሀን ዜጎች በመኖሪያ ቤታቸው በጥይት እና በከባድ መሳሪያ ተመተው ህይወታቸው ማለፉ ተሰምቷል።
የደብረ ታቦር ሆስፒትልም በከባድ መሳሪያ ተመቶ ጉዳት ደርሶበታል የተባለ ሲሆን ሁለት ታካሚዎችም ህይወታቸው አልፏል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአማራ ክልል ለስድስት ወራት የሚዘልቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል።
ክልሉ በወታደራዊ አመራር ቁጥጥር ስር ቢሆንም የክልሉ ምክር ቤት ባሳለፍነው ሳምንት አቶ አረጋ ከበደን ፕሬዝዳንት አድርጎ መምረጡ ይታወሳል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በትናትናው ዕለት ይፋ ባደረገው ሪፖርት ካሳለፍነው ሀምሌ ወር ጀምሮ በአማራ ክልል እየተካሄደ ባለው ጦርነት 183 ሰዎች ተገድለዋል ብሏል፡፡