በሶስት ባንኮች ላይ የ89 ሚሊዮን ብር ምዝበራ የፈጸመው ቡድን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ፌደራል ፖሊስ አስታውቋል።
ፖሊስ ዛሬ የካቲት 12 ቀን 2018 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ በሐሰተኛ የባንክ ዋስትና ሰነድ በመጠቀም በገዳ ባንክ፣ በኦሮሚያ ህብረት ሥራ ባንክ እና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ ከባድ የሙስና ወንጀል የፈጸሙ ተጠርጣሪዎችን ከነግብረ-አበሮቻቸው በቁጥጥር ሥር ማዋሉን አስታውቋል።
ተጠርጣሪዎቹ በተቀነባበረ ሴራ በአጠቃላይ ከ89 ሚሊዮን 296 ሺህ ብር በላይ በሀገር ኢኮኖሚ እና በባንኮች ላይ ጉዳት አድርሰዋል ተብሏል።
ተጠርጣሪው የጎደር ዋይን ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግል ማህበር ስራ አስኪያጅ ጌታሁን መለስ ሲሆን፣ ከገዳ ባንክ አገምሳ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አብዲሳ ቶሎሳ ጋር በጥቅም በመመሳጠር የቅርንጫፉን ፊርማና ማህተም ለወንጀል ተግባራቸው ሲጠቀሙበት መቆየታቸው ተገልጿል።
ዋነኛው ተጠርጣሪ ጌታሁን መለስ ከዚህ ቀደምም በኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ ላይ የ28 ሚሊዮን ብር እንዲሁም በንግድ ባንክ ላይ የ18 ሚሊዮን ብር የሐሰት ሰነድ ወንጀል ፈጽሞ ሲፈለግ የነበረ መሆኑ ታውቋል።
አበባው መኮንን የተባለ ሌላኛው ተጠርጣሪ ደግሞ ወንጀሉ እንዲፈጸም በማግባባትና ሁኔታዎችን በማመቻቸት ከፍተኛ የጥቅም ትስስር እንደነበረው ፖሊስ አረጋግጧል።
ፌደራል ፖሊስ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ አደጋ የሚደቅኑ ወንጀለኞችን የማደን ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል በመግለጽ፣ ህብረተሰቡ መሰል ህገወጥ ድርጊቶችን ሲመለከት በነፃ ስልክ መስመር 991 ወይም በ ‘EFPApp’ ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪውን አቅርቧል።