የቡና ግብይት ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ውጭ በስፋት እንደሚካሄድ ተገለጸ

ለውጭ ገበያ የማይውሉ ና የተመለሱ ምርቶች ግብይት በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ብቻ በኩል እንዲሸጡ አስገዳጅ አሰራር ቢዘረጋም ምርቶቹ መዳረሻቸዉ እየታወቀ አይደለም ተብሏል።

ከዉጪ ገበያ የሚመለሱት ምርቶች ግብይት በኢትዮጵያ ምርት ገበያ አማካኝነት መሆን እንዳለበት ቢቀመጥም ይህ ተግባራዊ እየተደረገ እንዳልሆነ ተገልጿል።

የፌደራል ዋና ኦዲተር እንዳስታወቀው ቡናን ጨምሮ ሁሉም ምርቶች መዳረሻቸዉ እየታወቀ አለመሆኑን ተናግሯል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ የምርት ቅበላ፣ ክምችት እና የግብይት ሥርዓት አፈፃፀምን በተመለከተ የተከናወነ የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ላይ ማብራሪያ ጠይቋል።

ከዉጪ ገበያዉ የሚመለሰዉን እና የማይወለዉን ምርት የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ሻጭ እና ገዥን የማገናኘት ሀላፊነት በግብይቱ ላይ እየታየ አይደለም ሲሉ የፌደራል ዋና ኦዲተር መሠረት ዳምጤ ገልፀዋል።

አንዳንድ ባለሀብቶች በተለይ የቡና ምርት  ከዉጪ ይልቅ የሀገር ዉስጥ ያዋጣቸዋል ያሉት ዋና ኦዲተር መሠረት ዳምጤ “በትክክለኛው አሰራር ግብይቱ በምርት ገበያዉ በኩል አልፎ እየሄደ ነዉ ወይ ? “ሲሉ ጠይቀዋል።

አያይዘዉም “የቡና ምርት አየር በአየር እየተሸጠ ይገኛል፣ በዚህም መንግስት ከፍተኛ ገቢ እያጣ ይገኛል” ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ቡና ላኪዎች ለውጭ ገበያ የማይውለውን የቡና ምርት ለተፈቀደላቸው የጅምላ ነጋዴዎች በሚሸጡበት ወቅት በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ብቻ እንደሚሸጡና እንደማይሽጡ የሚያረጋግጥበት ሥርዓት ዘርግቶ ክትትል የማያደርግ መሆኑ በሪፖርቱ ላይ ተጠቅሷል።

የቡና ምርት ላኪዎችም ቢሆኑ ለውጭ ገበያ የማይውለውን ምርታቸውን ወደ ምርት ገበያው በሚፈለገው ልክ እያመጡ አይደለም ተብሏል።

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መርጊያ ባይሳ በበኩላቸው የምርት መሸኛ ሰነድ በኤሌክትሮኒክስ መንገድ  እየተዘጋጀ ነዉ ብለዋል።

ጉምሩክ ኮምሽን በየኬላዉ መቆጣጠር እንዲችል የቡና እና ሻይ ባለስልጣንም የተመለሰዉ እና የተረፈዉ ምርት በአግባቡ ወደ ገበያ እየቀረበ ለሀገር ዉስጥ ፍጆታ እየተገበያየ ነዉ ወይ የሚለዉን እንዲከታተል የመረጃ ልዉዉጥ እንደተጀመረ ተናግረዋል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *