በአማራ ክልል ያለው ስደት አስደንጋጭ መሆኑ ተገለጸ

የአማራ ክልልን ለቆ ወደ ስደት እና ወደ ተለያዩ አካባቢዎች የሚፈልሰው የክልል ተወላጅ መጠን “አጅግ አስደንጋጭ ” መሆኑን የክልሉ ምክር ቤት አባላት ተናገሩ።

በአማራ ክልል ባለፉት 5 ወራት ወደ ትምህርት ገበታቸው የተመለሱ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች 36 በመቶ ብቻ መሆናቸውን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ተናግሯል።

ይህ የተነገረው የትምህርት ቢሮው የክልሉ ምክር ቤት መደበኛ ጉባዔ ላይ የ5 ወራት የስራ ክንውን ሪፖርቱን ባቀረበበት ወቅት እንደሆነ ሸገር ኤፍኤም ዘግቧል።

የምክር ቤቱ አባላት ለተማሪዎች በትምህርት ገበታ አለመገኘት ጦርነቱን፣ ስደት፣ የቀን ስራ፣ በትምህርት ተስፋ መቁረጥን ጨምሮ የተለያዩ ምክንያቶችን ዘርዝረዋል፡፡

በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ ወደ ትምህርት ያልተመለሱ ተማሪዎች አሁን በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ እንኳን መረጃ ማግኘት እንዳልተቻለ አስረድተዋል።

አንድ የምክር ቤት አባል የትምህርት መስኩ ችግር ውስጥ መሆኑን ጠቁመው በተለያዩ አካባቢዎች ከተማሪዎች ወላጆች እንኳን ልጆቹ የት እንዳሉ እንኳ መረጃ ማግኘት አንዳልተቻለ ተናግረዋል።

መረጃ ከሌለ ደግሞ እንዴት ነው እነዚህን ተማሪዎች መመለስ የሚቻለው? ሲሉ ጠይቀዋል።

በአማራ ክልል ከዚህ ቀደም የስደት ልማድ የሌለባቸው አካባቢዎች ሳይቀር አሁን ስደት ልምድ ሆኗል ተብሏል።

ይህም ልምምድ “በጣም አገደኛ ነው” ያሉት የምክር ቤት አባሉ ከክልሉ በስፋት “በአስራዎቹ ውስጥ ያሉ ወጣቶች ናቸው ዓባይ በረሃን የሚሻገሩት እነዚህ ወጣቶች እየተሰደዱ ያሉት ደግሞ ስለ ቸገራቸው ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም” ብለዋል።

አምራች የሆነው የሰው ሃይል ክልሉን ለቆ እየወጣ ነው፤ የሚሉት የምክር ቤት አባሉ ደጀን ከተማ ላይ “ለሁለት ሶስት ቀን ባደረግነው ምልከታ ባየነው ቁጥር በጣም ደንግጠናል “ሲሉ ተናግረዋል።

እነዚህ ልጆች ደግሞ በትምህርት በቅተው ስላልሆነ የሚሄዱት “የሰው ኬሻ ተሸካሚ እና እረኛ ነው የሚሆኑት” ብለዋል።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ በበኩሉ በአማራ ክልል ባለፉት 5 ወራት ወደ ትምህርት ገበታቸው የተመለሱ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች 36 በመቶ ብቻ ናቸው ብሏል።

ክልሉ በ5 ወራት ከቅድመ አንደኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ድረስ 7.4 ሚሊዮን ተማሪዎችን ለመመዝገብ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም ባለው የሰላም እጦት ምክንያት መመዝገብ የተቻለው 4.3 ወይንም 58.2 በመቶ ብቻ መሆኑን የቢሮ ሃላፊ አቶ ጥላሁን በሪፖርታቸው አመላክተዋል።

በዚህም የቅድመ አንደኛ ደረጃ ምዝገባ 85 በመቶ፣ በአንደኛ ደረጃ 58 በመቶ ፣ የሁለተኛ ደረጃ ደግሞ 36 በመቶ ብቻ መሆናቸውን አቶ ጥላሁን አስረድተዋል።

ወደ ትምህርት ቤት የሚሄዱ ተማሪዎች ምጣኔ ከባለፈው አመት ጋር ሲነፃፀር የተሻለ ቢሆንም በተለይ በጎጃም ዞኖች ችግሩ የከፋ እና የተመዝጋቢው መጠን 18 በመቶ ስለሆነ ልንወያይበት እና መፍትሔ ልንሰጠው ይገባል ብለዋል የትምህርት ቢሮ ሀላፊው።

ይህም በክልሉ ብቁ የሰው ሃይል ማፍራት እና ተወዳዳሪነት ላይ ከፍተኛ ስጋት ደቅኗል ተብሏል።

በአማራ ክልል በቀጠለው ወጊያ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ ስለ ወደሙ ተማሪዎች “በዳስ ስር ሆነው እንዲማሩ “ትዕዛዝ መስጠቱን ቢሮው ሃላፊ ተናግረዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ አረጋ ከበደ በበኩላቸው የክልሉ ትምህርት ችግር ውስጥ ያለ መሆኑን አስረድተዋል ከዚህን እንዴት መውጣት እንደሚቻል በትብብር መስራት ያሻል ብለዋል።

ለተማሪዎች በትምህርት ገበታ አለመገኘት ዋነኛው ችግር ግን ግጭትን ማድረግ ተገቢ እንዳልሆነ የተናገሩት አቶ አረጋ ከግጭቱ በፊትም ትምህርት በክልሉ ችግር ውስጥ የነበረ ዘርፍ መሆኑን አመላክተዋል።

ርዕሰ መስተዳድር አረጋ በክልሉ አለ ስለተባለው ከፍተኛ ስደት እና ፍልሰት ግን በክልሉ መገናኛ ብዙሃን በተላለፈው ስብሰባ ላይ ሃሳብ አልሰጡም።

የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ፋንቱ ተስፋዬ መክፈቻ ንግግራቸው የክልሉ ኗሪ ጦርነት መሸከም እንደሰለቸው ጠቁመው ታጣቂዎች ወደ ሰላም እና ንግግር እንዲመጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የቀጠለው ውጊያ በሁሉም ዘርፍ ላይ ቀውስ ማስከተሉን ያስተወሱት አፈ ጉባዔዋ ውጊያ የትም እንደማያደርስ ያለፉት 2 ዓመት ተኩል ጉዞ በቂ ማሳያ ነው ብለዋል።

በመንግስት የጸጽታ ሀይሎች እና የፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተካሄደ ያለው ጦርነት ሶተኛ ዓመቱን ሊይዝ ጥቂት ወራት ብቻ የቀሩት ሲሆን በርካታ ሀገራት እና የሰብዓዊ ተቋማት ተፋላሚ ሀይሎች ወደ ድርድር እንዲመጡ በተደጋጋሚ አሳስበዋል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *