ኢትዮጵያ ሁሉንም የስፖርት ውርርድ ቤቶች ፈቃድ ሰረዘች

በኢትዮጵያ ፈቃድ ተሰጥቷቸው ሲሰሩ የቆዩ የሁሉም የስፖርት ውድድር ውርርድ ድርጅቶች የሥራ ፈቃድ መሰረዙ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ሎተሪ አገልግሎት ሁሉንም የስፖርት ውድድር ውርርድ ድርጅቶች የሥራ ፈቃዶች ከታህሳስ 06 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ መሰረዛቸውን ገልጿል።

የፈቃድ ስረዛው በውርርድ እና በፋይናንስ ዘርፉ ላይ በተካሄደ አገር አቀፍ ጥልቅ ግምገማ ላይ ተመስርቶ የሕዝብን ጥቅም ለማስከበር የተወሰደ እርምጃ መሆኑን ድርጅቱ ገልጿል።

ውሳኔው በስራ ላይ ባሉትና ቀደም ሲል በይፋ በታገዱት በሁሉም የውርርድ ድርጅቶች በእኩልነት ተፈጻሚ ይሆናል ተብሏል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በሂደት ላይ ያለው ምርመራ በዘርፉ ውስጥ የተንሰራፋ ሀገ-ወጥ አሰራር፣ የፈቃድ ውል ጥሰት እና ለብሔራዊ ደህንነት ስጋት የሚሆኑ ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውሮች እንዳሉ በግልጽ አመላክቷል።

ለስፖርት ውርርድ ድርጅቶች እና ሲስተም ኦፕሬተሮች/አቅራቢዎች ከታሀሳስ 06 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአካል፣ በዲጂታል ወይም በሌላ መንገድ የሚካሄድ ማንኛውንም የውርርድ ሥራ እንዲያቋርጡ ትዕዛዝ ተሰጥቷል።

ሁሉም የገንዘብ ማስገቢያ መንገዶች  አገልግሎት መስጠት እንዲያቆሙም ታዟል የተባለ ሲሆን አዲስ የስፖርታዊ ውርርድ ፈቃድ መቀበልም ፈጽሞ አይቻልም ተብሏል።

ከሁለት ሳምንት በፊት ብሔራዊ ደህንነት አገልግሎት ስፖርታዊ አቋማሪ ድርጅቶች እና ሌሎች አካላት ጋር በመመሳጠር ከ100 ቢሎዮን ብር በላይ ገንዘብ አጭበርብረዋል ያላቸውን 24 ተጠርጣሪዎች በህግ ቁጥጥር ስር ማዋሉ ይታወሳል።

ተጠርጣሪዎቹ ከውጭ ዜጎች እና ህገወጥ የገንዘብ አዘዋዋሪዎች ጋር በመቀናጀት የሀገርን ደህንነት የሚጎዱ ወንጀሎችን እንደፈጸሙም ተገልጿል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *