በትግራይ ታጣቂዎች መካከል ያለው ውጥረት እንዳሳሰባቸው ነዋሪዎች ተናገሩ

በትግራይ ክልል መቐለ ከተማ ባለፉት ሶስት ቀናት የተፈጠሩ አለመረጋጋቶች ነዋሪዎችን እንዳስጨነቃቸው ተናግረዋል፡፡

ያነጋገርናቸው የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች እንዳሉት የትግራይ ታጣቂዎች ከነ ትጥቃቸው ወደ ከተማዋ በመግባት ሲንቀሳቀሱ የታዩ ሲሆን በተለይም የክልሉ ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት አካባቢ ያለው ሁኔታ አስፈሪ ነው ብለዋል፡፡

ለደህንነቱ በመስጋት ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ ነዋሪ እንዳለው ከሆነ “ከዚህ ቀደምም ብዙ አስተያየት ሰጥተናል፤ ሰሚ ግን የለም። ህዝቡ ጦርነት ሰልችቶናል ፤ እስካሁን ያደረጋችሁት የእርስ በርስ ግጭት ይበቃችኋል ብሏል። ገላጋይ ነው ያጣነው ” ብለዋል።

ከትናንት በስቲያ ጀምሮ የደመወዝ ይከፈለን የሚሉ ጥያቄዎችን ይዘው ወደ ከተማዋ ገብተዋል የተባሉት ታጣቂዎች ላለፉት ሁለት ቀናት የፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤትን እንደከበቡ ናቸውም ተብሏል፡፡

ታጣቂዎቹ ከከልሉ ፕሬዝዳንት ጸህፈት ቤት በተጨማሪም የክልሉ መንግስት ንብረት የሆኑት የድምፂ ወያኔ እና ትግራይ ቴሌቪዥን ሰራተኞችን በቢሯቸው በማባረር እንደተቆጣጠሩም ተገልጿል፡፡

በትናንትናው ዕለት በፕሬዝዳንቱ ጽህፈት አባካቢ ፍንዳታ እና የተኩስ ልውውጥ እንደነበር የአይን እማኞች የተናገሩ ሲሆን እስካሁን ስለጉዳዩ የወጣ መረጃ የሌለ ሲሆን በፍንዳታው የተጎዱ ሰዎች ይኑሩ አይኑሩ አልታወቀም፡፡

በትግራይ የተከሰተውን አለመረጋጋት ተከትሎ የሸቀጦች ዋጋ መጨመር፣ የገበያ አለመረጋጋት፣ ዳግም ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚሉ ስጋቶች እየጨመሩ መምጣታቸውም ነዋሪዎች እና ፖለቲከኞች በተደጋጋሚ በመናገር ላይ ናቸው፡፡

የፌደራል መንግስትን ጨምሮ ክልሉ መንግስት ኮሙንኬሽን እና ጸጥታ ቢሮዎች በጉዳዩ ዙሪያ ያወጡት መግለጫ የሌለ ሲሆን ጥያቄ ካቀረቡ ታጣቂዎች ጋር ውይይት በመደረግ ላይ መሆናቸውን ገልጸው ውይይቱ እንዳለቀ መረጃ እንደሚሰጡ ገልጸዋል፡፡

የህወሃት ታጣቂዎች በሀገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን እዝ ላይ ድንገተኛ ጥቃት ማድረሳቸውን ተከትሎ በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመት የዘለቀ ደም አፋሳሽ ጦርነት መካሄዱ ታወሳል፡፡

ጦርነቱ ትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልል የተካሄደ ሲሆን ከ500 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን ህይወታቸውን ሲያጡ 20 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ንብረትም እንደወደመ የገንዘብ ሚኒስቴር በወቅቱ ይፋ የደረገው ሪፖርት ያስረዳል፡፡

ጦርነቱ በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ሰላም ስምምነት የተፈረመ ሲሆን የስምምነቱ ፈራሚዎች የሆኑት ህወሃት እና የፌደራል መንግስት አንዳቸው ሌላኛቸውን ስምምነቱን ጥሰዋል የሚሉ ክሶችን በተደጋጋሚ ሲያቀርቡ ነበር፡፡

ላለፉት 60 ዓመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ዋነኛ ተጽዕኖ ፈጣሪ የነበረው ህወሃት በምርጫ ቦርድ መታገዱ እና ለሁለት መከፈሉን ተከትሎ በትግራይ ዳግም ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚሉ ስጋቶችን ፈጥሯል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ህወሃት ከኤርትራ ጋር ያልተገባ ግንኙነት በመመስረት በኢትዮጵያ ያሉ የትጥቅ ትግል የሚያደርጉ ታጣቂዎችን እንደሚደግፍ በፌደራል መንግስት ክስ ቀርቦበታል፡፡

ምርጫ ቦርድ ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ የፊታችን ግንቦት ወር ላይ ለማድረግ በዝግጅት ላይ ሲሆን የህወሃት ህጋዊነት ካልተመለሰ በትግራይ ምርጫ እንደማይካሄድ ባሳለፍነው ሳምንት መግለጹ ይታወሳል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *