የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት በገንዘብ ችግር ምክንያት ለመዘጋት የተቃረቡ መደበኛ መገናኛ ብዙኃንን ለመታደግ እና የነፃ ሚዲያ ድምፅ እንዳይቋረጥ የሚያግዝ የመገናኛ ብዙኃን የገንዘብ ድጋፍ ቋት (የሚዲያ ፈንድ) ለማቋቋም የሚያስችል ውይይት ማካሄዱን አስታውቋል።
“የሚቋቋመው ፈንድ ለግልና ለሕዝብ የሚዲያ ተቋማት የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋል” የተባለ ሲሆን፤ በተለያየ ምክንያት ከሥራ ውጪ በመሆናቸው ገቢያቸው የተቋረጠ ጋዜጠኞችን መታደግ ላይ እንደሚሰራም ተገልጿል።
የምክር ቤቱ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ታምራት ኃይሉ ባቀረቡት ጥናት፤ በርካታ የሚዲያ ተቋማት በአሁኑ ወቅት በሕትመት ወጪ መናር፣ በሳተላይት ክፍያ ውድነት እንዲሁም በሠራተኞች ደመወዝና የአስተዳደር ወጪ መናር ምክንያት ህልውናቸው አደጋ ውስጥ መግባቱን አብራርተዋል።
አቶ ታምራት እንደገለጹት፤ በሰለጠኑት ሀገራት የአንድ ሚዲያ መዘጋት እንደ አንድ ተቋም መዘጋት ሳይሆን በሚሊዮኖች ድምፅ መዘጋት ተደርጎ በመወሰዱ፣ ሚዲያዎች የሕዝብን ድምፅ ከማሰማት እንዳይስተጓጎሉ ልዩ ድጋፎችና ማበረታቻዎች ይደረጉላቸዋል።
በሌሎች ሀገራት የተቋቋሙት የሚዲያ ቋቶች፤ የሚዲያ ሥራዎች እንዳይቋረጡ በማድረግ የጋዜጠኞችን ከሥራ መባረርን እንደሚያስቀርም ጠቅሰዋል።
በዚህም መሠረት፤ ፈንዱ የሚዲያዎችን ታማኝና ገለልተኛ መረጃ ለሕዝብ እንዲያደርሱ የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ፣ ሕትመት ያቋረጡ ጋዜጦች ወደ ሕትመት እንዲመለሱ እንዲሁም ከሳተላይት ላይ የወረዱ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ወደ ስርጭት እንዲመለሱ ማድረግ አስፈላጊ ነውም ብለዋል።
የሚዲያ ፈንዱ በመንግሥት፣ በባለድርሻ አካላት ወይም በጋራ ትብብር ተቋቁሞ ሊተዳደር እንደሚችል የገለጹት አቶ ታምራት፤ የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ በመጥቀስ አብራርተዋል።
የፈንዱ የፋይናንስ ምንጮች መንግሥትን፣ ዓለም አቀፍ ለጋሾችን፣ የግሉን ዘርፍ እንዲሁም ሌሎች የገቢ ማስገኛ መንገዶችን ሊያካትቱ እንደሚችሉም በውይይቱ ላይ ተመላክቷል።
ፈንዱ ሥራ ሲጀምር፣ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ሚዲያዎች የመለየትና የወሰዱትን ገንዘብ ለታሰበለት ዓላማ ስለማዋል የክትትል ሥራ እንደሚሠራ ተገልጿል።
ጥናቱ የሚዲያ ፈንድ በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ውስጥ በማቋቋም መንግሥት በአስቸጋሪ ጊዜ ሚዲያዎችን የሚደግፍበትን አቅጣጫ አመላክቷል።
ምክር ቤቱ በየሁለት ሳምንቱ በተከታታይ በሚያዘጋጀው “ኢንተር ሚዲያ ዲያሎግ” (በመገናኛ ብዙኃን ተቋማት መካከለኛ ውይይት) ላይ ይህ አጀንዳ በስፋት ከተወያየበት በኋላ፤ እቅዱ ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ቀርቦ በቀጣይነት ወደ ሥራ የሚገባበት መንገድ እንደሚፈለግ ተገልጿል።
ይሁንና ሚዲያዎችን ከመክሰም ይታደጋል የተባለው ፈንድ መቼ ጀምሮ እንደሚቋቋም እና ወደ ስራ እንደሚገባ የተገለጸ ነገር የለም፡፡